የፊቼ ጫምባላላ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር በጋራ መስራት ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የፊቼ ጫምባላላ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር በጋራ መስራት ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2017 (ኢዜአ)፦ የፊቼ ጫምባላላ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች ከነሙሉ ይዘታቸው ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር በጋራ መስራት እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ለሲዳማ ህዝብ የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ላይ እንዳሉት የዘመን መለወጫው የተራራቁ ተሰባስበው ከዘመን ዘመን በሠላም ላሸጋገረ ፈጣሪ ምስጋና በማቅረብና መጪው ዘመንም የሰላም፤ የአንድነትና የበረከት እንዲሆን በመመኘት በጋራ የሚያከብሩት የአብሮነትና የምስጋና በዓል ነው፡፡
ፊቼ ጫምባላላ የመላው የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ መመዝገብ የቻለ የኢትዮጵያ የጋራ ሃብት መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉ በሲዳማ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝቦች መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጎልበት በህብረት የጋራ ልማትንና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያለው አንድምታ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
አባቶች ጠብቀው ያቆዩትንድንቅ እሴት ለህዝቦች የጋራ ልማትና ዕድገት ፋይዳው የጎላ በመሆኑ፤ የበዓሉን ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች እናኩነቶች ከነሙሉ ይዘታቸው ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉ የሰላም፣ የመተሳሰብ፤ የፍቅር እና የአንድነት እንዲሆን ተመኝተዋል።