የድርቅ ተጋላጭ አካባቢዎችን የመጠጥ ውሃ ለማዳረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የድርቅ ተጋላጭ አካባቢዎችን የመጠጥ ውሃ ለማዳረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው

ሀሮ ዱማል፤መጋቢት 18/2017 (ኢዜአ)፦የድርቅ ተጋላጭ አካባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውኃን ተደራሽ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
በባሌ ዞን በርበሬ ወረዳ ከ212 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በ'ዋተር ኤይድ ኢትዮጵያ' እና በመንግሥት በጀት የተገነባው ባለብዙ መንደር የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ አቶ አበራ እንደሻው እንዳሉት፥ መንግሥት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ባልሆኑባቸውና የድርቅ ተጋላጭ አካባቢዎችን ለማዳረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።
የመጠጥ ውሃን ለሁሉም አካባቢዎች በፍትሐዊነት ለማዳረስ እየተደረገ በሚገኘው ጥረትም ተደራሽነቱ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዚህም በአገር ደረጃ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን አንስተው፥ 'ዋተር ኤይድ ኢትዮጵያ' በበርበሬ ወረዳና ሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎች ያስገነባቸው ፕሮጀክቶች የዚሁ ጥረት አካል መሆናቸውን ገልጸዋል።
የ'ዋተር ኤይድ የኢትዮጵያ' ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ መተና በበኩላቸው መንግሥት የንጹህ መጠጥ ውኃን ለሁሉም ዜጎች ለማዳረስ እያደረገ የሚገኘውን ጥረት ድርጅቱ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ጋር በመቀናጀት የመጠጥ ውሃ ተደረሻነትን የሚያሻሽሉ በርካታ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በበርበሬ ወረዳ ከ41 ሺህ 600 የሚበልጡ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገው የበርበሬ ወረዳ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም የዚሁ ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል።
ባለብዙ መንደር የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ፕሮጀክቱ 33 ኪሎ ሜትር የመስመር ዝርጋታ፣ 18 የውኃ ቦኖዎች ግንባታና፣ ሶስት የውኃ ማጠራቀሚያ ጋኖች ግንባታዎችን ማካተቱን አስረድተዋል።
በተጨማሪም የመጠጥ ውሃ ፕሮጄክቱን ተደራሽነትና ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ የፀሐይ ኃይል የተገጠመለት መሆኑንም አክለዋል።
የውኃ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውኃን ተደራሽ ከማድረግ በተጓዳኝ በጤና ተቋማትና በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚታየውን የሥነ ንፅህና ባህሪ በማሻሻል ረገድ ትልቅ ዕገዛ ያለው መሆኑን አመልክተዋል።
የልማት ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ በባሌ ዞን የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ያመለከቱት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሐኪም አልይ ናቸው፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቱ በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የበርበሬ ወረዳ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየትም ፕሮጀክቱ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግራቸውን እንደፈታላቸው በመጠቆም ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት የተሳተፉ አካላትን አመስግነዋል።
በፕሮጀክቱ ምረቃ መርሃ ግብር ላይ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር የተጋበዙ አጋርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።