ጉባኤው ወጣቶች የበለጸገችና ሰላሟ የተረጋገጠ አፍሪካን በመገንባት ሂደት ሚናቸውን ይበልጥ እንዲያጎለብቱ የሚያግዝ ነው -ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤መጋቢት 18/2017 (ኢዜአ)፦የፓን አፍሪካ ወጣቶች አመራር ጉባኤ ወጣቶች የበለጸገችና ሰላሟ የተረጋገጠ አፍሪካን በመገንባት ሂደት ሚናቸውን ይበልጥ እንዲወጡ እንደሚያስችል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

የፓን አፍሪካ ወጣቶች አመራር ጉባኤ ከመጋቢት 25 እስከ 27/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድም ተገልጿል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፤ አፍሪካ ከህዝቧ አብዛኛው ወጣት መሆኑን ያነሱ ሲሆን ፥ በጠንካራ ማህበራዊ እሴቶች፣ጥበባትና በተፈጥሮ ጸጋዎች የታደለች አህጉር ናት ብለዋል።

ጉባኤው “የወጣቶችን አቅም ለበለፀገች አፍሪካ” በሚል መሪ ሃሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ይህ አህጉራዊ ጉባኤ ዋና አላማ ወጣቶች የበለጸገችና ሰላሟ የተረጋገጠ አፍሪካን በመገንባት ሂደት ውስጥ የመሪነት ሚናቸውን እንዲያበረክቱ ለማስቻል መሆኑን ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ወጣቶች ቻርተር ላይ የተደነገጉ መብቶችና ግዴታዎችን ለማስገንዘብም ጉባኤው ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን ለወጣቱ ለማስረጽና በአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባዔ የተያዘው አህጉራዊ መሻቶችን በጋራ እውን ለማድረግ ነው ብለዋል።

የወጣቶችን ዲፕሎማሲ አቅም በማሳደግ ወጣቱ ከሀገሩ አልፎ በአህጉርና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የአፍሪካን መብትና ጥቅም ማስከበር እንዲችል ጉባዔው ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል ፡፡

መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የወጣቱን ጉዳይ የዕቅዳቸው አካል አድርገው በመስራት ረገድ ለመወያየት ምቹ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት የነጻነትና የለውጥ ምሳሌ ናት ያሉት ሚኒስትሯ፥ ለአፍሪካ አንድነትና ትስስር መጠናከር ከፍተኛ ሚና እያበረከተች ያለች ሀገር መሆኗን አንስተዋል።

የፓን አፍሪካን እሳቤ በመላው አፍሪካ እንዲጎለብት የወጣቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ውጤቶች እየተመዘገቡበት የሚገኘው የመደመር እሳቤ ለፓን አፍሪካኒዝም መጎልበት በሚኖሩ እሴቶች ላይ የፓናል ውይይት እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያ ታሪክና እሴት የሚተዋወቅበትና በመዲናዋ የተሰሩ ልማቶች የሚጎበኙበት እንዲሁም የባህል ልውውጥ የሚደረግበት ፕሮግራም እንደሚኖርም ጠቁመዋል።

በመድረኩ ከ53 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ አንድ ሺህ የሚሆኑ ወጣት መሪዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣የተለያዩ መንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ የወጣት አደረጃጀቶች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እንደሚሳተፉ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም