አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ የዕውቀት፣ የሥነ-ጥበብና የኪነ-ጥበብ ቤት ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ የዕውቀት፣ የሥነ-ጥበብና የኪነ-ጥበብ ቤት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዝዳንቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ ፈለገ ሰላም የሥነ-ጥበብ እና ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤቶችን ጎብኝተዋል።


 

ጉብኝታቸውም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ጥበብና ሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤቶች ለዘርፉ ዕድገት እያበረከቱት ያለውን ሚና እና የስራ እንቅስቃሴያቸው ላይ ምልከታ ማድረግን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

የአለ ፈለገ ሰላም የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት በአፍሪካ ደረጃ ከሚገኙ የሥነ-ጥበብ ተቋማት አንፃር ከፍ ያለ ዕውቀት የሚንሸራሸርበት ተቋም መሆኑን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቱ ለሥነ-ጥበብ ስራ እና ለመማር ማስተማር ምቹ መደላድል የሚፈጥር የከባቢ ልማት እና ዘመናዊ ተቋም እየተገነባ እንደሚገኝም አንስተዋል።

ለረጅም ጊዜ ተጠብቀው የቆዩ የትምህርት ቤቱ የአዕምሮ ውጤቶች አስገራሚ ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ ለዚህም ለዩኒቨርሲቲው አመራር፣ መምህራንና ተማሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።

የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤትም ለኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ዕድገት የራሱን ጉልህ አሻራ ያሳረፈ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ለሙዚቃ ስራ ያለን ዋጋ ከፍ ያለ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ ይህም ለኪነ-ጥብብ ዕድገት አበክረው የሰሩ ኢትዮጵያውያን የልፋት ውጤት መሆኑን አስገንዝበዋል።


 

በኢትዮጵያ የሙዚቃታሪክ ውስጥ ከድምጻውያን ባሻገር የመሳሪያ ተጫዋችና ተወዛዋዦች ተገቢውን ክብርና ዕውቅና ማግኘት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፥ ዩኒቨርሲቲው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መርሃ ግብሮች በማቀናጀት በኪነ-ጥበብና ሥነ-ጥበብ ዘርፍም ሚናውን እየተወጣ ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በዩኒቨርሲቲው የኪነ-ጥበብና ሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤቶች ያደረጉት ጉብኝትም ስኬቶችን ለማስቀጠልና ጉድለቶችን ለማስተካከል ስንቅ መሆኑን አስረድተዋል።

የአለ ፈለገ ሰላም የሥነ-ጥበብና የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያና የዓለም የሥነ-ጥበብና የኪነ-ጥበብ ሥራዎች ላይ ተጠቃሽ የሆኑ በርካታ የጥበብ ሰዎችን እያፈሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም