የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅሞች ለማስተዋወቅ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ ኢንቨስትመንትን ለማነቃቃት የሚያስችል የሚዲያ አጋርነት እና የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ገጽታ ለማጠናከር ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፥ ኮሚሽኑ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሽግግር በመምራት ሂደት ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት እድሎች ማስተዋወቅ ቀዳሚ ስራው መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት ለኢንቨስትመንት ምቹ ምህዳር በመፍጠር በርካታ ተግባራትን ማከናወኑንም አስረድተዋል።
እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች ወደ ሥራ የገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን የመደገፍ እና የመከታተል ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እነዚህን ተግባራት በአግባቡ ለማስተዋወቅ የሚዲያ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፥ ስምምነቱ እምቅ አቅሞችን ለመጠቀም የሚያግዝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የኢንቨስትመንት መረጃዎችን በሙያዊ እውቀትና በጥራት ተደራሽ በማድረግ ግንባር ቀደም መሆኑን አንስተው ከአገልግሎቱ ጋር በመስራታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው ስምምነቱ የኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻነት ለማስፋት እንደ ትልቅ እድል የሚወሰድ ነው ብለዋል።
አገልግሎቱ የኮሚሽኑ ህልሞች እውን እንዲሆኑ በዜናና ዜና ነክ የዘገባ ስራዎች የማስተዋወቅ ሚናውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
ለዚህም የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ዕድሎች፣ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን እና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ተደራሽ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።