የመተባበርና የመተጋገዝ እሴትን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም እና አብሮነት በጋራ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የመተባበርና የመተጋገዝ እሴትን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም እና አብሮነት በጋራ መስራት ይገባል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 18/2017 (ኢዜአ)፦የመተባበርና የመተጋገዝ እሴትን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም እና አብሮነት በጋራ ልንሰራ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሞሮኮ ንጉስ መሀመድ ስድስተኛ የአፍሪካ ዑላሞች ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ለአንድ ሺህ አቅመ ደካሞች ማዕድ አጋርቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፥በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ኔዛ አሎዩ ምሃምዲ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ እንዳሉት፥ የመተባበርና የመተጋገዝ እሴትን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም እና አብሮነት በጋራ መስራት ይገባል።
በረመዳን ጾም ለአቅመ ደካሞች የሚደረገውን የድጋፍ ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ነው የገለጹት።
የሞሮኮ ንጉስ መሀመድ ስድስተኛ የአፍሪካ ዑላሞች ፋውንዴሽን ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፥ ሁላችንም ባለን አቅም መደጋገፍ አለብን ሲሉ አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ ተቋማትን በማስተባበር በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞችን ጨምሮ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የኢፍጣር መርሃ ግብር ሲያካሂድ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ኔዛ አሎዩ ምሃምዲ በበኩላቸው፥ ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉ ለኢትዮጵያ ያለንን ቅርበትና ወዳጅነት የሚያሳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ፋውንዴሽኑ ከተቋቋመ አንስቶ በተለያዩ አገራት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች እያገዘ እንደሚገኝ በመጠቆም ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ሞሮኮ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነትና ትብብር የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ ሞሮኮ በማህበራዊ እና ሰብዓዊ ትብብሮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
እገዛውን ያገኙ ወገኖች ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው የረመዳን ወር ሁሉም ለሰላም የሚተጋበትና ባለው አቅም የተቸገሩትን የሚረዳበት ነው ብለዋል።