ባንኩ እያደገ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት የሚያሟሉ አዳዲስ የፋይናንስ አገልግሎቶች ማቅረቡን ያጠናክራል- አቤ ሳኖ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 18/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያደገ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት የሚያሟሉ አዳዲስ አስተማማኝ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ ዓለም አቀፍ የዲጂታል ክፍያዎችን ማድረስ የሚያስችሉ ፕላስቲክ እና ቨርቹዋል ቅድመ ክፍያ ማስተር ካርዶችን ዛሬ ይፋ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ ባንኩ የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት በዲጂታል ፋይናንስ ላይ ትኩረት ያደረጉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ከዚህም መካከል አዳዲስ አስተማማኝ የፋይናንስ ዲጂታል ቅድመ ክፍያ አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ ለማቅረብ እያከናወነ የሚገኘውን ተግባራትን አንስተዋል፡፡

ባንኩ ዛሬ ይፋ ያደረገው ዓለም አቀፍ ፕላስቲክ እና ቨርቹዋል ቅድመ ክፍያ ካርዶች አዳዲስ እና አስተማማኝ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለደንበኞች ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡

ዲጂታል የቅድመ ክፍያ ካርዶች በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ነጋዴዎች ተቀባይነት ያላቸው መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፥ ክፍያ ካርዶች የባንኩን የላቀ የደህንነት እርምጃዎች የሚያሳዩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይ ባንኩ እያደገ የመጣውን የደንበኞች ፍላጎት ለመመለስ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ የዓለም አቀፍ ዲጂታል ክፍያዎችን ተደራሽ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የማስተር አፍሪካ ፕሬዝዳንት ማርክ ኤሊዮት በበኩላቸው፤ በንግድ ባንክ ይፋ የተደረገውን የቅድመ ክፍያ ዲጂታል ማስተር ካርድ በታዳጊ የአፍሪካ ገበያዎች ለማሳደግ ለያዘው ስትራቴጂ ቁልፍ ምዕራፍን እንደሚከፍት አስታውቀዋል።

ከንግድ ባንክ ጋር በመሆን ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲሳተፉ የሚያስችላቸው አስተማማኝ ዲጂታል የክፍያ መፍትሄ መቅረቡ የሚያኮራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በቀጣይ ማስተር ካርድ ከባንኩ ጋር ዲጂታል ቴክኖሎጂን የማሳደግ ስራ ላይ በጋራ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም