የፊቼ ጫምባላላ በዓል በሰላም እንዲከበር ከጸጥታ ሀይሉ ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው-የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የፊቼ ጫምባላላ በዓል በሰላም እንዲከበር ከጸጥታ ሀይሉ ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው-የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች

ሀዋሳ፤መጋቢት 18/2017 (ኢዜአ) :- የሲዳማ የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል በሰላም እንዲከበር ከጸጥታ ሀይሉ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የፊቼ ጫምባላላ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁንም የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት ፊቼ ጫምባላላ የሰላም፣የአብሮነት፣የመረዳዳትና የፍቅር እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር እየሰሩና በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን በመቀበል ላይ ናቸው።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል የባህል አዳራሽ ክፍለ ከተማ ሐረር ቀበሌ ነዋሪ አቶ እንዳለ ተመስገን እንዳሉት፥ የፊቼ ጨምበላላ በዓልን በሰላም ለማክበር በቀበሌ ደረጃ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
ቀደም ባሉት ቀናት ነዋሪዎቹ ከተማዋን ማጽዳታቸውንና ዛሬ ደግሞ በሲዳማ ባህል መሰረት እንግዶችን ''ዳኤ ቡሹ'' በማለት እየተቀበሉ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ሄለን ተክለሀይማኖት በበኩሏ እንግዶች የእንግድነት ስሜት ሳያድርባቸው በዓሉን አክብረው እስኪመለሱ ድረስ በመልካም ሁኔታ ለማስተናገድ ተዘጋጅተን እየጠበቅን ነው ብላለች።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መልካሙ አየለ እንዳሉት፥ የሲዳማ የዘመን መለወጫ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል።
የከተማዋ የፖሊስ ኃይል ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አስቀድሞ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀው፥ በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶች በዓሉን በሰላም እንዲያከብሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ ለ24 ሰዓት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሲዳማ የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል ዛሬና ነገ በሀዋሳ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።