በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሳታፊና ጤናማ ፉክክር የሚታይበት የፖለቲካ አውድ እየተፈጠረ ነው

አሶሳ፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ):- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር በመፈጠሩ አሳታፊና ጤናማ ፉክክር የሚታይበት የፖለቲካ አውድ እየተፈጠረ መሆኑን የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

የምክርቤቱ ሰብሳቢና የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን) ፓርቲ ሊቀመንበር አብዱሰላም ሸንገል፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተለይም በክልሉ ያለውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በክልሉ 10 የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የጠቀሱት አብዱሰላም፤ የዚህ ተሳትፎ መሰረቱ የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋና በሃሳብ የበላይነት በክርክር የሚያምን ትውልድ እየተፈጠረ በመምጣቱ መሆኑን ተናግረዋል።

ከለውጡ በፊት የተፎካካሪ ፓርቲ አደረጃጀቱን ለማስፋት ከባድ ፈተና እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ የፖለቲካ ፓርቲ የመደራጀትና አባላትን ማፍራት የሚችልበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

በክልሉ ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር በመፈጠሩ አሳታፊና ፉክክር የሚታይበት የፖለቲካ አውድ እየተፈጠረ ይገኛልም ነው ያሉት።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ በሀሳብ እየተከራከሩ አብሮ የመስራት ልምድ እየዳበረ ስለመሆኑም አንስተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋነኛ ዓላማ የህዝብን አንድነት ማጠናከር፣ የሀገሪቱን ሰላምና ልማትን ማስቀጠል መሆኑን ጠቅሰው በሀገር ብሄራዊ ጥቅምና ሉአላዊነት ላይ ልዩነት ሊኖር አይገባም ብለዋል።

በክልሉ የመንግስት ኃላፊነት ላይ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ስልጣን ይዘው እየሰሩ መሆኑንና ለአብነትም እሳቸው የካቢኔ አባል እንደሆኑ ገልጸዋል።

የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ከክልሉ መንግስት ጋር ውይይት ለማድረግ በሚፈልግበት ጊዜ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን እና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በንግግር እየፈቱ መሆኑንም ተናግረዋል።

የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃሳብ እና ሰላማዊ መንገድን ተጠቅመው ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም