ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር በቁርጠኝነት እየሰራች ነው-አምባሳደር ባጫ ደበሌ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 18/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአፍሪካ ህገወጥ የቀላል መሳሪያ ዝውውር ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ ገለጹ።

አምባሳደር ባጫ ደበሌ ከቀጣናዊ የቀላል የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ማዕከል ዋና ፀሐፊ ጂን ፒዬር ቤቲንዲጅ ጋር ዛሬ በናይሮቢ ተወያይተዋል።

ውይይቱ ማዕከሉ በቀጣናው ህገ ወጥ የቀላል የጦር መሳሪያዎች እና አነስተኛ ትጥቆች ዝውውር የመቆጣጠር አቅሙን ማሳደግ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።

አምባሳደር ባጫ ኢትዮጵያ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ቁርጠኝነት እንዳላት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ህገወጥ የአነስተኛ ጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው ጥረት ያላትን ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል አመልክተዋል።

የቀጣናዊ የቀላል የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ማዕከል (RECSA) ዋና ፀሐፊ ጂን ፒዬር ቤቲንዲጅ  ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው እና አፍሪካ ህገ ወጥ የቀላል የጦር መሳሪያዎች ዝውውር በመቆጣጠር ጥረቶች ውስጥ ቁልፍ  አጋር መሆኗን በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ የህገወጥ መሳሪያ ዝውውር ቁጥጥር ማድረግ ለደህንነት እና ዘላቂ ልማት መረጋጋጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው በጽኑ እንደምታምንም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም