በዞኑ የበጋ መስኖ ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የበጋ መስኖ ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ መጥቷል

አምቦ፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን የበጋ መስኖ ልማት የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ ምምጣቱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በጽህፈት ቤቱ የአዝእርት ልማትና የእጽዋት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ደጀኔ ገመቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ አርሶ አደሩ የዝናብ ወቅትን ጠብቆ ከማምረት ወጥቶ በበጋ መስኖ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት መስራቱን ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ በተለይም በበጋ መስኖ አትክልትን በማልማት ኢኮሚያዊ ተጠቃሚነቱን ከማሳደግ ባለፈ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ መድረጉን ጠቅሰዋል።
በዞኑ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውኃ ሀብትን በመጠቀም ዘንድሮ በበጋ መስኖ በመጀመሪያው ዙር 30ሺህ 164 ሄክታር መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት 3ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
ባህላዊና ዘመናዊ የመስኖ አውታሮችን በመጠቀም ጎመን፣ ሽንኩርት፣ ሰላጣ፣ ቲማቲም፣ ካሮት፣ ድንችና ስኳር ድንች መልማታቸውን አንስተዋል።
በሁለተኛ ዙርም 9ሺህ 224 ሄክታር መሬት በማልማት 4 ሚሊዮን ኩንታል የአትክልት ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በበጋ መስኖ ልማቱ ከተሰማሩት አርሶ አደሮች መካከል የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ነዋሪ አቶ አለሙ ፈይሳ፤ የውሀ አማራጮችን በመጠቀም በመስኖ ያለሙትን ቀይ ሽንኩርትና ቲማቲም ለገበያ በማቅረብ ከ250ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
የአምቦ ወረዳ አርሶ አደር በቀለ መገርሳ በበኩላቸው በመጀሪያው ዙር በመስኖ ካለሙት የጓሮ አትክልት ሽያጭ 300ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።
በሁለተኛ ዙርም የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን ማልማት መጀመራቸውን አክለዋል።