በከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በመሳተፍ ሰርተን በቆጠብነው ገንዘብ የተሻለ ገቢ እያመነጨን እንገኛለን - የአክሱም ከተማ ተጠቃሚዎች

አክሱም፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ)፡- በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በመሳተፍ የሥራና የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ የተሻለ ገቢ እያመነጩ መሆናቸውን በአክሱም ከተማ በፕሮግራሙ የታቀፉ ነዋሪዎች ገለጹ።

በከተማው ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያ 112 ሚሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን ከ6ሺህ በላይ ነዋሪዎችም ከሚከፈላቸው የወር ደመወዝ ላይ በመቆጠብ እና ተጨማሪ ብድር በመውሰድ በጀመሩት ስራ የተሻለ ህይወት እንዲመሩ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል።

ወይዘሮ አባዲት አስመላሽ በከተማው በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በሥራ ላይ እንደሚገኙ ተናግረው በየወሩ ከሚከፈላቸው 3ሺህ ብር የተወሰነውን በመቆጠብና በወሰዱት ተጨማሪ ብድር 50 ጫጩቶችን ገዝተው ወደ ዶሮ እርባታ ስራ መግባታቸውን ገልፀዋል።   

በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥም የ300 ዶሮዎችና የአንዲት የወተት ላም ባለቤት መሆን መቻላቸውን ገልጸው፣ ዛሬ ላይ የተበደሩትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ መልሰው አምስት ልጆቻቸውን ሳይቸገሩ እያስተማሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ሌላኛዋ የአክሱም ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ማሚት ወልደ ገብርኤል በፕሮግራሙ በመሳተፋቸው ሥራን፣ የቁጠባ ባህልንና ከአነስተኛ ገንዘብ በመነሳት ኑሮን ማሸነፍ እንደሚቻል ልምድ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

በ20ሺህ ብር የጀመሩት የዶሮ እርባታ ቁጥር አንድ መቶ በማድረስ የእርባታ ስራውን እያቀላጠፉ መሆኑን ተናግረዋል።

በየወሩ ከሚሰጠው ሶስት ሺህ ብር 20 በመቶውን በመቆጠብ ከጓደኞቹ ጋር በመተባበር ከተማውን አቋርጦ ከሚወርደው ወንዝ ውሃ በመጥለፍ የመስኖ ልማት መጀመራቸውን የገለጸው ደግሞ ወጣት አስማረ ትኩእ ነው።

28 አባላትን አደራጅቶ ወደ መስኖ ልማት የገባው የእነ አስማረ ማህበር የጓሮ አትክልት እያመረቱ ለገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ተናግሯል።

የማህበሩ አባል ወይዘሮ ለታይ ገብረመድህን በበኩላቸው፣ የመስኖ ልማት ስራ ከጀመሩ ወዲህ አራት ልጆቻቸውን ከማስተማር ባለፈ የመኖርያ ቤት መገልገያ ቁሳቁሶችን ማሟላት መቻላቸውን አመልክተዋል።

የአክሱም ከተማ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሮ ለተሚካኤል ኪዳነማርያም፣ በከተማው በመጀመሪያው ዙር 6ሺህ 293 ሰዎች ተመልምለው ወደ ሥራ መሰማራታቸውና ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ 112 ሚሊዮን ብር መመደቡን ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ በየወሩ ከሚከፈላቸው ገንዘብ ቀንሰው በመቆጠብ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እየተሳተፉ ናቸው ያሉት አስተባባሪዋ፣ የዕለት ኑራቸውን ከማሸነፍ አልፈው አነስተኛ ሃብት ማፍራት ጀምረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም