ቀጥታ፡

የስደትና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት አምስት ተሽከርካሪዎችን ለጋምቤላ ክልል ሰጠ

ጋምቤላ፤ መጋቢት 18/2017 (ኢዜአ) ፡-የስደትና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያገኛቸውን አምስት ተሽከርካሪዎች ለጋምቤላ ክልል ድጋፍ አደረገ። 

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን ድጋፉን ለክልሉ መንግስት ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን ተቀብሎ በማስጠለል ረገድ እንደ አብነት የምትጠቀስ አገር ናት።

ስደተኞችን በማስጠለልና ያለውን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት በማጋራት የሰብዓዊ ድጋፍና ጥበቃ እያደረጉ ካሉ ክልሎች መካከል ደግሞ ጋምቤላ ክልል አንዱ ነው ብለዋል። 

በመሆኑም የክልሉ መንግስት ስደተኞችን ተቀብሎ እያደረገ ላለው ሰብዓዊ ድጋፍና ጥበቃ ስራዎች መቃናት አገልግሎት መስሪያ ቤቱ የጀመራቸውን ልማታዊ ድጋፎች አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

አገልግሎቱ ከተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ያገኛቸውን አምስት ተሽከርካሪዎች ድጋፍ ማድረጉ የዚሁ ጥረት አካል መሆኑንም አብራርተዋል ። 

በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ተጠሪ ሚስተር አንድሪው ሚቦጎሪ ( Mr, Andrew Mibogori) ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት በርካታ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ረገድ እያደረገች ያለው ጥረት የሚመሠገን ተግባር ነው ብለዋል። 

በተለይም የጋምቤላ ክልል መንግስት ከ380 ሺህ በላይ ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል። 

ኮሚሽኑ ስደተኞችንና ስደተኛ ተቀባይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የትምህርትና ሌሎችም የልማት ዘርፎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል። 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት ክልሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች ተቀብሎ በማስጠለል ሰብዓዊ ድጋፍና ጥበቃ እያደረገ ይገኛል። 

ክልሉ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ለስደተኞቹ በማጋራት የተቻለውን ሁሉ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በቀጣይም የተጀመሩ ድጋፎች ይቀጥላሉ ብለዋል። 

በዕለቱ ድጋፍ የተደረጉት ተሽከርካሪዎች በክልሉ ለሚካሄዱ የትምህርት፣ የግብርና፣ የአካባቢ ጥበቃና ሌሎች ድህነት ቀናሽ የልማት ስራዎችን ለማሳለጥ ያግዛል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም