በቦረና ዞን የተገነቡ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ - ኢዜአ አማርኛ
በቦረና ዞን የተገነቡ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2017 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተገነቡ በፀሐይ ሃይል የሚሰሩ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።
በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት አካል ከሆኑት ፕሮጀክቶች መካከል 100 ኩዩቢክ ሜትር ሪዘርቬየር ያለው የሮምሶ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ106 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር በላይ በሚሆን ወጭ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ፕሮጀክቱ ከአራት ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እና 27 ሺህ በላይ የሚሆኑ እንስሳቶችን ውሃ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የቦረና ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ በሪሶ ጋኖ በዞኑ በስድስት ወረዳዎች ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ፕሮጀክት ድርቅ ቢከሰት ህብረተሰቡ እንዳይፈናቀልና የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ ለፕሮጀክት ግንባታው ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በተያያዘ ዜና በቦረና ዞን ከ131 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተገነባ ያለው የዲዳ ያቤሎ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እና በዞኑ ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ውጪ የተገነባው የኤርደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ተገልጿል።
ሁሉም የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በሶላር ኢነርጂ እንደሚሰሩ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።