በዞኑ የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም ለማሳደግ የሚያስችል የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት እየተዘጋጀ ነው

ጭሮ ፤መጋቢት 18/2017 (ኢዜአ)፡-በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም ለማሳደግ የሚያስችል የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት በማዘጋጀት ለመስኖ ልማትና ለበልግ አዝመራ ጥቅም ላይ  እየዋለ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የግብርና ቴክኖሎጂ ማስፋፋትና አፈር ለምነት ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ታሪኩ አሰፋ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት መንግስት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የአርሶ አደሩ የማምረት አቅም እየጨመረ መጥቷል።

በተለይ እየጨመረ የመጣውን የአርሶ አደሩን የማዳበሪያ ፍላጎት ለማሟላት በአካባቢው የሚገኙ ጸጋዎችን ተጠቅሞ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያመርት ሰፊ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም በዚህ ዓመት ብቻ በዞኑ 15 ወረዳዎች የሚገኙ ከ400 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት በስፋት ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመት የተዘጋጀውን ከ14 ሚሊዮን ሜትር ኩዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ 300 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው ሲሆን አርሶ አደሩ ለመስኖ ልማትና ለበልግ አዝመራ ጥቅም ላይ እያዋለው መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለፃ በዚህ ዓመት የተዘጋጀው ኮምፖስት ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ከ7 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ብልጫ አለው።

በዞኑ ጭሮ ወረዳ ጃርሶ ቀበሌ አርሶ አደር ሙሜ ጠሀ በሰጡት አስተያየት የፋብሪካ ማዳበሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋው እየጨመረ በመምጣቱ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በስፋት ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በመሆኑም በዚህ አመት ከ100 ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበርያ በማዘጋጀት ለበልግ አዝመራ ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም  ለኬሚካል ማዳበሪያ የሚያወጡትን ወጪ ከመቀነስ ባለፈ ምርታማ እንደሚያደርጋቸውም ተናግረዋል።

በወረዳው የጃርሶ ቀበሌ አርሶ አደር አህመድ አሊዪ በበኩላቸው በባለሙያዎች ምክር በመታገዝ በአጭር ጊዜ የሚደርስ ኮምፖስት በማዘጋጀት ጥቅም ላይ እያዋሉ መሆኑን ገልፀዋል።

ዘንድሮ ባዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበርያም በጉድጓድ ውሃና አነስተኛ መስኖ የጓሮ አትክልት  በማልማት ከምርት ሽያጭ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል። 

የተፈጥሮ ማዳበሪያ የአፈር ለምነትን የሚጨምር መሆኑን በተግባር አረጋግጠናል የሚሉት አርሶ አደሮቹ በቀጣይም ስራውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም