በምስራቅ ቦረና ዞን በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ከ44 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ተመቻቸ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ከ44 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ተመቻቸ

ነገሌ ቦረና ፤ መጋቢት 18/2017 (ኢዜአ)፦በምስራቅ ቦረና ዞን በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራትከ44 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መመቻቸቱን የዞኑ የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በጽህፈት ቤቱ የእቅድ ክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ ሊበን ሀለኬ በዞኑ በበጀት ዓመቱ 66 ሺህ 500 ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስምንት ወራት 44 ሺህ 561 ወጣቶች ወደ ስራ የገቡ ሲሆን፤ ከዚህም መካከል ሴቶችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡
አቶ ሊበን ሀለኬ እንዳሉት የስራ እድል ፈጠራውም በማዕድን ማውጣትና ግብይት፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግንባታና በሸቀጣ ሸቀጥ አገልግሎት መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች 693 ሄክታር የማምረቻ ቦታ፤ 13 የመሸጫ ሼዶችና ሁለት የእርሻ መኪናዎች ድጋፍ መደረጉንም ሃላፊው ጠቅሰዋል፡፡
ለስራ ዘርፎቹ አንቀሳቃሾች ከሲንቄ ባንክና ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት 78 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ብድር መሰጠቱንም አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ወጣቶቹ በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ለተጠቃሚዎች ምርትና አገልግሎታቸውን እያቀረቡ ነው ብለዋል።
እንዲሁም በዞኑ በዚህ ዓመት ወደ ስራ ለሚገቡ ወጣቶች የብድር አገልግሎት እና የማምረቻና የመሸጫ ቦታ መመቻቸቱን አስታውቀዋል፡፡
ከስራ እድሉ ተጠቃሚ ወጣቶች መካከል የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪ ናትናኤል ለማ ከአራት ባልደረቦቹ ጋር በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ መሰማራቱን ተናግሯል፡፡
ወጣቱ ባለፉት ስምንት ወራት የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑን ገልጾ፤ በዚህም በገቢው እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከመርዳት አልፎ እየቆጠቡ መሆኑንም ተናግሯል።
ወጣት ናትናኤል እንዳለው የመሸጫ ሱቅ ድጋፍና የብድር አገልግሎትም ተመቻችቶላቸዋል፡፡
የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሙክታር ኡመር በበኩሉ መንግስት ያመቻቸላቸው የመስሪያ ቦታና የብድር አገልግሎት በራስ አቅም ሰርቶ መለወጥ የሚያስችል ነው ብሏል፡፡
ለወጣቱና አራቱ ባልደረቦቹ ከነገሌ ከተማ አስተዳደር የ360 ሺህ ብር ብድርና የመሸጫ ሱቅ ድጋፍ መመቻቸቱንም ገልጿል፡፡
"ድጋፉ ወጣቶች ባለን እውቀትና ክህሎት ሰርተን እንድንለወጥ፤ ምርትና አገልግሎትን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ለሌሎችም እንድንተርፍ ያስችለናል" ብሏል፡፡