ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብቷን ለማሳካት እያደረገች ያለውን ጥረት ማጠናከር ይገባናል - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብቷን ለማሳካት እያደረገች ያለውን ጥረት ማጠናከር ይገባናል - ምሁራን

ድሬዳዋ/ሆሳዕና፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብቷን የዲፕሎማሲ አማራጭን በመጠቀም ለማሳካት እያደረገች ያለውን ጥረት ማጠናከር ይገባናል ሲሉ ምሁራን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በባህር በር ዙሪያ ሰሞኑን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
በዚህ ላይ በመመሰረት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በድሬዳዋ እና በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩ ምሁራንን አነጋግሯል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ ህግ መምህር አለምሰገድ ደጀኔ እንዳሉት፤ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተሰራው የተቀናጀ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ የባህር በር ጥያቄን ለማሳካት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
ለሶስት አስርት ዓመታት የተዳፈነው የሀገራችን የባህር በር የማግኘት አለም አቀፍ መብት በይፋ የአደባባይ አጀንዳ መደረጉ ወሳኝ እርምጃ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሀገራችን በተባበሩት መንግስታት ህግ መሰረት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር የማግኘት መብቷ የተረጋገጠ መሆኑንም አንስተዋል።
የተጀመረውን ጥረት በተጠናና በተቀናጀ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች የአለም አጀንዳ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ምሁሩ ጠቁመው፤ ለዚህም የሀገራችን የአለም የዲፕሎማቲክ ማዕከል መሆኗ፣ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባለቤትነትና ለአለም ሰላም መከበር እያበረከተች ያለችው ታላቅ ስራ ጥሩ መደላድሎች ይሆናሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት መብት ለማሳካት የአሁኑ ትውልድ እና ምሁራን ዋና አጀንዳ ማድረጉን አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉም አብራርተዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ አስራት ኤርሞሎ(ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በሴራ የባህር በር ባለቤትነቷን እንድታጣ መደረጉን አስታውሰው፤ መንግስት የትውልዱ ጥያቄ የሆነውን ይህን ጉዳይ በዲፕሎማሲ አማራጭ ለማሳካት የጀመረውን ጥረት ማጠናከር አለበት ብለዋል፡፡
የሀገር ደህንነት ስጋትን ከመታደግ ባለፈ ከውጪ ለሚገቡ ምርቶች የሚወጣን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ በማስቀረት የሀገሪቱን ዕድገት ለማፋጠንና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ለመገንባት የባህር በር ባለቤትነት አይተኬ ሚና እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡
መንግስት የባህር በር የማግኘት ጥረትን በሰላማዊ መንገድ ተፈፃሚ እንዲሆን እያደረገ ስላለው ጥረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መግለፃቸው ተገቢ ያልሆኑ አስተያየቶችና ውዥንብሮችን ያረመና ያጠራ መሆኑንም አውስተዋል፡፡
ሰላማዊና ዲፕሎማሲ አማራጮችን በመጠቀም ሀገሪቱ የባህር በር ማግኘት የምትችልባቸው ሰፊ አማራጮች እንዳሏት ጠቁመው የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር ይገባናል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር እየተነሱ ካሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ እንደሆነ የተናገሩት በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉዓለም ኃይለማርያም ናቸው።
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት የውጪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የገቢና ወጪ ንግድን ለማሳለጥ የባህር በር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ የሆነው የአንካራው ስምምነትን ጨምሮ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ጉዳይ ዓለም አቀፍ አጀንዳ እንዲሆንና የበርካታ ዓለም ሀገራትን ድጋፍ እያገኘ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡