በማእከላዊ ጎንደር ዞን ገበያን የማረጋጋት ተግባር እየተከናወነ ነው

ጎንደር፤ መጋቢት 18/2017 (ኢዜአ)፡- በማእከላዊ ጎንደር ዞን የምርት አቅርቦትን በማሻሻል ገበያን የማረጋጋት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ሃላፊ አቶ አይቸው ታረቀኝ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ገበያን ለማረጋጋት እንዲቻል ለምርት አቅርቦት ስራ የሚውል ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡

በምርት አቅርቦትና ስርጭት ሂደትም ዩኒየኖች፣ የሸማቾች ማህበራትና ኢንተርፕራይዞች እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል ። 


 

በሸማቾች ማህበራትና በነጋዴዎች በኩል ባለፉት ሁለት ወራት ከ33ሺ ኩንታል በላይ የግብርና ምርቶች ማቅረብ መቻሉን ጠቅሰዋል ።

ከቀረቡት የግብርና ምርቶች መካከልም ጤፍ፣ በቆሎና ማሽላ እንደሚገኙበት ጠቁመው ከገበያ ዋጋ በኩንታል ከ200 እስከ 400 ብር ቅናሽ እንዳላቸውም አመልክተዋል።

መጪውን የረመዳንና የትንሳኤ  ጾም ፍቺ ምክንያት በማድረግም ለህብረተሰቡ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማቅረብ የሚያስችሉ ዝግጅቶች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በአላቱን  ምክንያት በማድረግ ከ270ሺ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ጨምሮ አንድ ሺ 325 ኩንታል ስኳር፣ 368 ኩንታል የዳቦ ዱቄትና 7ሺ ኩንታል ሽንኩርት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የሚያስችል ስራ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡

በዞኑ ዘጠኝ የወረዳ ዋና ከተሞችም ሸማቹንና አምራቹን በቀጥታ ለማገናኘት የሚያስችሉ የንግድ ትርኢትና ባዛሮችን ለማዘጋጀት ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል ።

በከተሞች የሚታየውን የዋጋ ንረትና የምርት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለነዋሪዎች እየቀረቡ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የጸሃይ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ የኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ ይሁኔ ዳኘው ናቸው፡፡


 

ዩኒየኑ ጤፍን ጨምሮ 71ሺ ኩንታል የተለያዩ የምግብ ሰብሎችን ከአርሶአደሩ በመግዛት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ መጀመሩን ተናግረዋል ።

እስካሁንም ከ7ሺ ኩንታል በላይ ጤፍ  በኩንታል  ከገበያ ዋጋ እስከ 400 ብር ቅናሽ በማድረግ መቅረቡን ተናግረዋል ።

ዩኒየኑ ባቋቋመው የምግብ ዘይት ፋብሪካ ያመረተውንና ከአዲስ አበባ ከሚገኙ አምራች ድርጅቶች ያስመጣውን ከ370ሺ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ገበያውን በማረጋጋት የድርሻውን ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡


 

የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ታምሩ በላይና አቶ እሸቴ መንግስቴ በዩኒየኑ በኩል ጤፍና የምግብ ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘታቸውን ጠቁመው የቀረበው ምርት ገበያውን በማረጋጋት በኩል ድርሻው የላቀ መሆኑን አመልክተዋል ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም