መንግስት ጠንካራና እና በአግባቡ የተደራጀ የፋይናንስ ስርአት በመዘርጋት የመንግስት ሃብት ለሃገራዊ ልማት እንዲውል እያደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት ጠንካራና እና በአግባቡ የተደራጀ የፋይናንስ ስርአት በመዘርጋት ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች የሚሰበሰብ ሃብት ለሃገራዊ ልማት እንዲውል እያደረገ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ኤፍ ኤስ ዲ ኢትዮጵያ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ነጠላ ሂሳብ አስተዳደር "ለመንግስት ገንዘብ አስተዳደር አስፈላጊ መሳሪያ" በሚል መሪ ሃሳብ አውደ ጥናት እያካሄደ ነው። 

በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝን ጨምሮ የኤፍኤስዲ የቦርድና የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ በዚሁ ወቅት መንግስት የገንዘብ እንቅስቃሴውን ለማዘመን በጀመረው ጥረት ሂደቱን በዲጂታል ስርአት ለመለወጥ አበረታች ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የመንግስትን ሃብት ወጪ ቆጣቢ ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ ስርአት ማስተዳደር ሀገራዊ ግዴታችን ነው ብለዋል።

መንግስት ጠንካራና እና በአግባቡ የተደራጀ የፋይናንስ ስርአት በመዘርጋት ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ፣ ከእርዳታ ፣ ከብድር እና ከሌሎች ምንጮች የሚሰበሰብ ሃብት በአግባቡ ለሃገራዊ ልማት እንዲውል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የትሬዥሪ ነጠላ አካውንት ስርአት ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።

የትሬዠሪ ነጠላ አካውንት ስርአት በበርካታ የባንክ ሂሳቦች ተበታትነው የሚገኙ የመንግስት ገንዘቦችን ወደ አንድ ቋት የሚያመጣ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም በተበታተነ የሂሳብ አያያዝ የሚከሰቱ ችግሮችን በማቃለል ዘመናዊ የመንግስት ጥሬ ገንዘብ አያያዝ አስተዳደር እንዲኖር አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል  ብለዋል።

ዘመናዊ የመንግስት ጥሬ ገንዘብ አያያዝ ደግሞ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ግልፅ እንዲሁም ተጠያቂነት የሰፈነበት የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር እንዲኖር ያስችላል ነው ያሉት። 

ይህም መንግስት ለአጭር ጊዜ ብድሮች የሚያወጣቸውን ወጪዎች በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ጠቅሰዋል። 

እንዲሁም የተናበበ የገንዘብና ፊሲካል ፖሊሲ እንዲኖር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ነው የጠቀሱት።

ለነጠላ ገንዘብ አስተዳደር ትግበራ ዘላቂነትና ውጤታማነት በተለይም የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም