በፈጠራ በሰራው ማሽን የወዳደቁ የውሃ ፕላስቲኮችንና ጠርሙሶችን ፈጭቶ ዳግም አምርቶ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ያለው ወጣት

የ32 ዓመቱ ወጣት ዳዊት ተክለኃይማኖት ተወልዶ ያደገው ሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱንም በዚያው ተከታትሎ 10ኛ ክፍል ሲደረስ በሽሬ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በአውቶሞቲቭ በደረጃ አራት ተመርቋል። በተመረቀበት ሙያም የመኪና ጥገና ስራ ተቀጥሮ ለአራት ዓመታት ሰርቷል።


 

ዳዊት ከልጅነቱ እስከ እድገቱ ጎበዝ፣ ስራ ወዳድ፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚሞክር ታታሪ መሆኑን የሚያውቁት ሁሉ ይናገራሉ። በዚሁ መንገድም እየሰራ እራሱንና ቤተሰቡን እያገዘ በታታሪነቱ ቀጥሏል።

በአንድ አጋጣሚ በሚኖርበት አካባቢ ጥቅም ላይ ውለው በተጣሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶች የተደፈነ የውሃ ማፋሰሻ ቦይ ሲከፈት ይመለከታል፤ ወዲያውኑም ከወዳደቁ የፕላስቲክ ውጤቶች ምን መስራት ይቻላል የሚለውን ጥያቄ በውስጡ አሰላሰለ።


 

የፕላስቲክ ውጤቶች ወደ ጥቅም እንደሚቀየሩ በአንድ ወቅት ከቅርብ ጓደኛው መስማቱ ትዝ አለው። በጊዜው ስለ ጉዳዩ ሰምቶ በውስጡ ደጋግሞ ከማሰብ ውጪ አማራጭ አልነበረውም። የጎርፍ መውረጃ ቦይን በመዝጋት ችግር እየፈጠረ ያለን የፕላስቲክ ቁስ ወደ ጥቅም የመቀየር ሃሳብን ሲያወጣና ሲያወርድ ከረመ።

የሚኖርባት ሽሬ ከተማ ሞቃታማ በመሆኗ ነዋሪው በተለምዶ የታሸገ ውሃ ተጠቅሞ የሚጥለው ፕላስቲክ በብዛት ስላለ የጥሬ ዕቃ ችግር እንደማይገጥመው አረጋግጧል።

በመሆኑም ሙሉ ትኩረቱን የትም ተጥለው የሚገኙትን የፕላስቲክ ውጤቶች የሚፈጭ ማሽን ማፈላለግ ላይ አደረገ።  ማሽኑንም ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ አቀና። ዳዊት በወቅቱ የፈለገው ሁለት ዓይነት ማሽኖችን ነበር፤ አንደኛው የፕላስቲክ ውጤቶቹን የሚፈጭ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ አጥቦ ለዳግም ጥቅም የሚያዘጋጅ። 

ሆኖም የማሽኑ ዋጋ ውድና ካለው ካፒታል አንጻር የማይሞከር ሆኖ አገኘው፤ በመሆኑም ወደ ሽሬ ከተማ በመመለስ ማሽኑን ራሱ ከወዳደቁ ብረቶች በመስራት ከሁለት ዓመት በፊት ስራ አስጀመረ።


 

ማሽኑን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሃያ ሁለት ቀናት ብቻ እንዳስፈለጉት የገለፀው ወጣት ዳዊት በተበደረው አንድ ሚሊዮን ብር ስራ መጀመሩን ይናገራል።

ከወዳደቁ ብረቶች በሰራው ማሽን የወዳደቁ የውሃ ፕላስቲኮችንና ጠርሙሶችን ፈጭቶና አምርቶ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ያለው ወጣት በስራው ስኬታማና ትርፋማ ሆኖ ሌሎችንም ቀጥሮ በማሰራት ላይ ይገኛል። በዚሁ ስራው ቤተሰቦቹን በማስተዳደር ላይ ይገኛል።

ከስራ ጅማሬው በአንድ ዓመት ውስጥ ከአንድ ሺህ ኩንታል በላይ የተፈጨ የፕላስቲክ ውጤቶችን ለሀገር ውስጥና ለቱርክ ገበያ በማቅረብ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ገልጿል።

በአንድ ሚሊዮን ካፒታል የተጀመረው ስራ በአሁኑ ወቅት ወደ 20 ሚሊዮን ብር ከፍ ማለቱን የገለፀው ዳዊት አሁን ላይ ለ67 ወገኖች የስራ ዕድል በመፍጠር ለወርሃዊ የደመወዝ ክፍያም ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያደርግ ተናግሯል።

የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወጣት ሰላም ማሞ፤ በተፈጠረላት የስራ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን ከራሷ አልፋ ቤተሰብ እያስተዳደረች መሆኑን ተናግራለች። የዳዊት ስራ ወዳድነትና ባለመታከት ለውጤት የመብቃት ጥረት ለብዙ ወጣቶች ምሳሌ እንደሚሆንም ተናግራለች።

ቆሻሻ ጥቅም እንዳለው የተማርኩበት ስራ ነው በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ እስጢፋኖስ ገብረመድህን በወር 11 ሺህ 500 ብር እየተከፈላቸው ቤተሰባቸውን እያስተዳደሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በየወሩ በማገኘው ደመወዝ ቤተሰቤን ለማስተዳደር ችያለሁ ያለችው ደግሞ አበባ በረኸ ነች።

የዳዊት የጥረት ውጤት ከራሱ አልፎ ለብዙዎቻችን ስራ ያስገኘና ለቤተሰባችንም መተዳደሪያ በመሆኑ ልናመሰግነው እንወዳለን ብለዋል።

የከተማዋ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት አስተባባሪ አቶ አብራሃለይ ፍቃዱ በበኩላቸው የወጣቱን የስራ እንቅስቃሴ ለማበረታታት ስራውን አስፍቶ እንዲሰራ የሚያደርገው የመሬት አቅርቦት እንደሚመቻችለትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም