የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶቹ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን መፍትሄ የሚሰጡ ናቸው - የምስራቃዊ ሲዳማ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶቹ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን መፍትሄ የሚሰጡ ናቸው - የምስራቃዊ ሲዳማ ዞን ነዋሪዎች

ሀዋሳ፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል የምስራቃዊ ሲዳማ ዞን የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድጉ የምስራቃዊ ሲዳማ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን መልካም አስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የጀመራቸው የመንገድ፣ የድልድይና የውሃ ፕሮጀክቶች ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸው መፍትሄ የሚሰጡ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የቡራ ወረዳ ነዋሪ አቶ በቀለ ዱሹሼ ቀደም ሲል በአካባቢው የሚስተዋለው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ይህንን ችግር ለመቅረፍ የገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የአካባቢውን ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦች ችግር የቀረፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጨቤ ጋምቤልቱ ወረዳ ነዋሪው አቶ ገናሌ ፍጡንጌ በበኩላቸው ቀበሌያቸውን ከወረዳ ጋር የሚያገናኘው ድልድይ በመገንባቱ ቀደም ሲል የነበረውን የትራንስፖርት እጥረት መፍታቱን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ምርታቸውን ለገበያ ለማቅረብና የግብርና ግብዓቶችን ለማጓጓዝ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡
በወረዳው እየተሰራ ያለው የመንገድና የድልድይ ግንባታ ዘርፈ ብዙ ችግራቸውን እንደሚቀርፍ የተናገሩት ደግሞ የአሮሬሳ ወረዳ ነዋሪው አቶ ንጉሴ ቦጋለ ናቸው፡፡
የሲዳማ ክልል መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ታፌ በበኩላቸው እስከ በጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ከ1ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የገጠር መንገዶች ግንባታና ጥገና ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ 261 ኪሎ ሜትሩ የገጠር መንገድ ግንባታ ሲሆን ቀሪው ጥገና መሆኑን ጠቅሰው ለፕሮጀክቶቹ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ከመንገድ ፕሮጀክቶቹ በተጨማሪ ዘንድሮ በልዩ ትኩረት ከተጀመሩ 12 የድልድይ ግንባታ ፕሮጀክቶች አራቱ የተጠናቀቁ ሲሆን ቀሪዎቹ እስከ በጀት ዓመቱ ማብቂያ ይጠናቀቃሉ ብለዋል፡፡