ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መከላከያ ኢኒሼቲቮች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለበት - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መከላከያ ኢኒሼቲቮች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለበት - ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየተገበሯቸው ላሉ ሀገር በቀል ኢኒሼቲቮች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
በጀርመን በርሊን ከተማ እየተካሄደ ያለው የ2025 የፒተርስበርግ የአየር ንብረት ለውጥ ምክክር እንደቀጠለ ነው።
በመድረኩ ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ተጽእኖ ለመቀነስ እና ለመከላከል እየወሰደቻቸው ያሉ ሀገር በቀል እርምጃዎችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ስኬቶች በምክክሩ ላይ አድናቆት የተቸረው ሲሆን ኢኒሼቲቩ ሊደገፍ እና ሌሎችም ሀገራት ሊተገብሩት እንደሚገባ ተገልጿል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረበት እአአ 2019 ከነበረበት በ6 በመቶ ጨምሮ እአአ በ2023 የደን ሽፋኑ 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡
ኢኒሼቲቩ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ማህበረሰቦችን ኑሮ እና የአኗኗር ዘይቤ እንዲለወጥ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ገልጸዋል።
የፍራፍሬ እና የጥምር ደን ችግኞችን በመትከል አርሶ አደሮች አቮካዶን ጨምሮ የተለያዩ መርቶችን ኤክስፖርት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል።
መሰል ሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ተሞክሮዎች ተጽእኖውን ከመቀነስ ባለፈ የዜጎችን የኢኮኖሚ ፍላጎት መመለስ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና እያጋጠማቸው ላሉ ሀገራት ችግሩን ለመከላከል እየወሰዱት ላለው እርምጃ ፋይናንስን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን እንዲያደርጉም ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ከምክክሩ ጎን ለጎን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ልዩ አማካሪ ሴልዊን ሀርት ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም የሶስተኛው ዙር ብሄራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅድን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲ እቅድ ሂደት ላይ በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የማጣጣሚያ እቅዱን ከቀናት በፊት ይፋ ያደረገች ሲሆን እቅዱን በብራዚል ከሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ(ኮፕ 30) በፊት ለማስገባት እየሰራች መሆኑም ተጠቁሟል።
በውይይቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢትዮጵያ እ.አ.አ ሴፕቴምበር 2025 በምታዘጋጀው ሁለተኛ የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ መሳታፍ የሚችሉበትን መንገድ በጋራ ለማመቻቸት ከመግባባት ላይ መደረሱም ተገልጿል።
በተያያዘም ሚኒስትሯ ብሄራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማማጣሚያ እቅድ የድጋፍ ቡድን ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ፓብሎ ቪዬራ ጋርም ተወያይተዋል።
ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ የብሄራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ዕቅድ እና ትግበራ ውጤታማ እንዲሆንና ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በስኬት እንድታዘጋጅ ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
የ2025 የፒተርስበርግ የአየር ንብረት ለውጥ ምክክር በጀርመን እና ብራዚል መንግስታት የጋራ ትብብር የተዘጋጀ ነው።