ለጅቡቲ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ዝርጋታ ተከናወነ - ኢዜአ አማርኛ
ለጅቡቲ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ዝርጋታ ተከናወነ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ)፦ ለጅቡቲ ድንበር ተሻጋሪ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ዝርጋታ መከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቱ ዝርጋታ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ ሲከናወን መቆየቱንም አስታውቋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ 8 ሜጋዋት ኃይል፣ 36 ኪሎ ሜትር የመስመር ዝርጋታ እንዲሁም 8 ባለ 1250 ኬቪኤ ትራንስፎርመር ተከላ ተከናውኗል ብሏል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ኦንያድ የተሰኘው የጅቡቲ ውኃ ፕሮጀክት ባቀረቡት ተጨማሪ ኃይል ጥያቄ መሠረት ሁለተኛው ምዕራፍ ስራ መጠናቀቁን የአገልግሎቱ መረጃ ያመለክታል።
ለውኃ ፕሮጀክቱ 12 ነጥብ 2 ሜጋ ዋት ተጨማሪ ኃይል መጠየቁንና ከአዲጋላ ሰብስቴሽን ከሚወጣው መስመር 8 ሜጋ ዋት በ1250 ኬቪኤ 8 ትራንስፎርመሮች፤ ቀሪው 4 ነጥብ 2 ሜጋ ዋት ደግሞ በ28 ባለ 500 ኪቪኤ፣ 315 ኬቪኤ እና 400 ኪቪኤ ትራንስፎርመሮች ኃይል እንዲያገኝ ተደርጓል ሲልም ገልጿል።
ፕሮጀክቱ ካለው ሀገራዊ ፋይዳ አንፃር የአካባቢውን በርሃማ የአየር ፀባይ በመቋቋም ስራውን በስኬታማነት ማጠናቀቅ መቻሉንም አገልግሎቱ አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ የሁለተኛው ምዕራፍ ሥራ ተጠናቆ ርክክብ እየተደረገ እንደሚገኝም በመረጃው ተመልክቷል።