የሀረር ከተማ የመጀመሪያው ዙር ኮሪደር ልማት የኤሌክትሪክ መስመር ማዛወር ስራ ተጠናቋል- አገልግሎቱ - ኢዜአ አማርኛ
የሀረር ከተማ የመጀመሪያው ዙር ኮሪደር ልማት የኤሌክትሪክ መስመር ማዛወር ስራ ተጠናቋል- አገልግሎቱ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ)፡- በሀረር ከተማ እየተከናወነ ባለው የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት የመካከለኛና ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመር ማዛወር እና ማሻሻያ ስራ በተለዩ 18 ሳይቶች ላይ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
በዚህም በአጠቃላይ 1ሺህ 107 የእንጨት እና የኮንክሪት ምሰሶዎች፣ 40 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኤሌክትሪክ መስመር እንዲሁም 12 የተለያየ መጠን ያላቸው ትራንስፎርመሮች የማዛወር ስራ ተከናውኗል ብሏል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የመስመር ማዛወር ስራ የተከናወነው በሀረር ከተማ ከአራተኛ እስከ ስታዲየም፣ ከአጅፕ እስከ ሰላም አደባባይ፣ ከሀረር ቢራ እስከ ገስታውስ፣ ከአራተኛ እስከ ቀይ መስቀል እንዲሁም ከኢማም አህመድ ስታዲየም እስከ ገስታውስ የሚሸፍን መሆኑንም ጠቁሟል።
ቀደም ሲል የነበረው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በዋናነት ያረጀ በመሆኑ አካባቢዎቹ ላይ የኃይል መቆራረጥ ይከሰት የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ በተሰራው የማዛወር ስራ የኃይል መቆራረጥን በዘላቂነት ሊቀርፍ በሚችል መልኩ ደረጃውን የጠበቀ የመስመር ዝርጋታ ተከናውኗል ነው ያለው አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፡፡
በተጨማሪም በሁለተኛው ዙር በሚከናወነው የኮሪደር ልማት 1 ነጥብ 66 የመካከለኛ እና 2 ነጥብ 45 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መስመር የማዛወር ስራ የሚከናወን ሲሆን፤ በአጠቃላይ 523 የሚሆኑ የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች እና 4 የተለያየ መጠን ያላቸው ትራንስፎርመሮችን ለማዛወር የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቋል ሲልም አስታውቋል።
የሁለተኛው ዙር የመስመር ማዛወር ስራ የሚከናወነው በከተማዋ ከስላሴ ቤተክሰርስቲያን እስከ የሺመቤት ትምህርት ቤት፣ ከደሴ ሆቴል እስከ ሙጢ አደባባይ፣ አባድር ፕላዛ አካባቢ እስከ ቡዳ በር አካባቢዎች የሚከናወን ነው ብሏል በመግለጫው፡፡
በአጠቃላይ በኮሪደር ልማቱ እየተከናወነ የሚገኘው የኃይል መስመር ማዛወር ስራ በከተማዋ ለኮሪደር ልማት በተለዩ ዋና ዋና መስመሮች ላይ የሚኖረውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ከማዘመን ባሻገር የኃይል መቆራረጡን በዘላቂነት ለመቀነስ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑንም አመላክቷል፡፡