መንግስት ለዜጎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሰራ ነው - ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለዜጎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሰራ ነው - ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት ለዜጎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በአሜሪካ የስታንፎርድ ድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ልዑክ ጋር በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እና ዘላቂነት ያለው የጤና ስርአትን መገንባት በሚቻልበት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ በተለይ የእናቶችና ህጻናት ጤናን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት እንዲሁም ጠንካራ የጤና ስርዓትን ለመፍጠር እየተሰራ ያለውን ስራ በተመለከተ ሚኒስትሯ ገለጻ ማድረጋቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።
መንግስት ለዜጎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሻሻል ያለውን ቁርጠኝነትም ሚኒስትሯ ገልጸውላቸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን የጤና አጠባበቅ ሥርዓት አወቃቀር በማስመልከት የተለያዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃዎችን ማጠናከር ላይ ያተኮሩ ውጥኖችንም ለልዑኩ በዝርዝር መግለጻቸው ተመላክቷል።
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና ፕሮግራሞችን አስፈላጊነትና በሀገሪቱ የጤና አጠባበቅ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ያለውን ተነሳሽነትም እንዲሁ ማብራራታቸው በመረጃው ተገልጿል።
የልዑኩ አባላት በበኩላቸው የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎትንና ሌሎች የጤና አጠባበቅ ተቋማትን በመጎብኘት ስለ ሀገሪቱ የጤና መሠረተ ልማት መስፋፋት መረዳታቸውን መግለጻቸው ተጠቁሟል።