በክልሉ ለሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት በተሰሩ ስራዎች አንጻራዊ ሰላም ማስፈን ተችሏል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2017(ኢዜአ)፦ በክልሉ ለሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት በተሰሩ ስራዎች አንጻራዊ ሰላም ማስፈን ተችሏል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች ጋር በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ በወላይታ ሶዶ ከተማ ያደረጉት ምክክር ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ማጠቃለያ እንደገለፁት፤ ኢ-ተገማች በሆነው የአለም ሁኔታ ክልላዊ፤ ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታን ፈጥኖ በመረዳት ሁሌም ቀድሞ ለመገኘት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ለሰላምና ፀጥታው ዘርፍ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ስራዎች በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህም ክልሉ ከልማት ስራዎች ባሻገር ትልልቅ ሀገራዊ ኩነቶችን በስኬት ማስተናገድ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡

ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ በሰላም በኩል የተመዘገበው ስኬት የኢንቨስትመንት ፍሰትና የቱሪዝም ዘርፍን በከፍተኛ ሁኔታ በማነቃቃት ለፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ለዘላቂ ልማት ምቹ መደላድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም በክልሉ በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ለተመዘገበው አመርቂ ውጤት ህብረተሰቡ እና የፀጥታ ሀይሉ ሊመሰገኑ ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

ሰላም በጊዜና በቦታ ሳይገደብ ሁሌም የሁሉም ነገር ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ጠቁመው፤ የፖሊስ መኮንኖች ነፃና ገለልተኛ ሆነው፤ ሞያዊ ስነምግባሩን በተግባር በመላበስና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ህብረተሰቡን በቅንነት ማገልገል ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም ጊዜያዊና ወቅታዊ ፈተናዎችን በብቃት መሻገር የሚችል የፖሊስ ሰራዊት እና ጠንካራ ተቋም ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ከነባራዊ ሁኔታዎች አኳያ ዕቅዶችን መከለስ፤ በጠንካራ ተቋማዊ አሰራር መምራትና መፈፀም፤ ሞያዊ ስነምግባርን ጠብቆ ለሕግና ለሕገመንግስታዊ ስርዓቱ ታማኝ በመሆንና ከህብረተሰቡ ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ በመስራት የተጀመሩ የሰላም ግንባታ ተግባራትን ከግብ ማድረስ ይገባል ነው ያሉት።

የሽግግር ፍትህ ስራዎች ትግበራን መከታተልና የጠንካራ ተቋም ግንባታ ስራዎችን በማጠናከር የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የዲጂታል ዘመኑን በዋጀ አግባብ የሰላምና ፀጥታውን ዘርፍ የመረጃ ስርዓት ማዘመንና በነባራዊ ሁኔታዎች ግምገማና ሳይንሳዊ የመረጃ ትንተናን መሠረት ባደረገ መልኩ ህግ የማስከበር ዝግጁነትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

የሚዲያ አውታሮችን በህዝቦች መካከል ጥርጣሬን፤ ጥላቻንና ግጭትን ለመቀስቀስ በመጠቀም የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ በሚሰሩ አካላት ላይ ህጋዊ አስተማሪ ዕርምጃዎችን በመውሰድ የህግ የበላይነትን በሁሉም መስክ በሙላት ለማረጋገጥ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ገቢ ፍታሃዊ ግብር በመሰብሰብ የልማት ስራዎችን በራስ አቅም ለመሸፈን መስራት የሁሉም የጋራ ኃላፊነት በመሆኑ ገቢ አሰባሰብ ስራዎችን በማገዝ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሀገር በቀል የሰላም ግንባታ ተቋማትንና ህዝባዊ አቅሞችን በአግባቡ በመጠቀም በቀጣይም የክልሉን ሰላም ለማፅናት መስራት እንደሚገባም አክለዋል።

በአጠቃላይ የፖሊስ ሀይሉ ከተሰጠው በላይ በመስራትና ከሚጠበቀው በላይ ፈፅሞ በመገኘት በታሪክ ተወዳሽ ለመሆን ሀላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባ አቅጣጫዎች ማስቀመጣቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም