ሚኒስቴሩ በነዳጅ አጠቃቀም የቴክኖሎጂ ሥርዓት ለሌሎች ተቋማት አርዓያ መሆን አለበት - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ በነዳጅ አጠቃቀም የቴክኖሎጂ ሥርዓት ለሌሎች ተቋማት አርዓያ መሆን አለበት - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፡- የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር በነዳጅ አጠቃቀም የቴክኖሎጂ ሥርዓት ለሌሎች ተቋማት አርዓያ መሆን እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
በሒሳብ ኦዲት ግኝት ላይ ሚኒስቴሩ የወሰዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች የሚያበረታቱ መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።
ቋሚ ኮሚቴው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴርን የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት ሪፖርት የእርምት እርምጃን ገምግሟል።
ቋሚ ኮሚቴው በንብረት አስተዳደር፣ በሒሳብ ብልጫና ማነስ የተመዘገቡ የኦዲት ግኝት ጉድለቶችን አስመልክቶ ጥያቄዎችን በጽሁፍ አቅርቧል።
በዚሁ ወቅት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ የንብረት አስተዳደር፣ ሒሳብ ብልጫና ማነስ የኦዲት ጉድለቶችን ለማስተካከል የወሰደው የእርምት እርምጃ በበጎ የሚታይ ነው።
ገቢና ወጪን፣ ቋሚና አላቂ ዕቃዎችን በቴክኖሎጂ ሥርዓት ለማስተዳደር የተጀመረው ስራ አበረታች ቢሆንም ቀጣይነት ያለው ስራ የሚጠይቅ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር የነዳጅ አጠቃቀም ሥርዓት ለሌሎች መስሪያ ቤቶች አርዓያ መሆን የሚያስችለውን ስራ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር አቶ አበራ ታደሰ፤ ሚኒስቴሩ በማነስና መብለጥ የተመዘገቡ የቅድመ ክፍያ፣ የማያዣ፣ የእሴት ታክስና ጥሬ ገንዘብ ግኝቶችን ማስተካከሉን አረጋግጠዋል።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) በንብረት አስተዳደር፣ በማነስና መብለጥ የተመዘገቡ የሒሳብ ጉድለቶች ላይ ቀጣይነት ያለው የእርምት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።
የተቋሙ ተሽከርካሪዎች የነዳጅ አጠቃቀምን ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የመረጃና ግብይት ሥርዓት ለማስገባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ በበኩላቸው፤ የንብረት አስተዳደር፣ የወጪና ገቢ ሒሳብ አያያዞችን በተቀናጀ የዲጂታል ሥርዓት ማድረግ የሚያስችል መሰረተ ልማት እየተፈጠረ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ(ዶ/ር)፤ የሒሳብና ንብረት አስተዳደር ጉድለቶችን ለማሻሻል በተደረገው ጥረት ልክ በነዳጅ አጠቃቀም ሥርዓት ላይ ለተቋማት አርዓያ መሆን አለበት ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ለተቋማት ምሳሌ የሚሆን ከሰው እጅ ንክኪ የገንዘብ ገቢና ወጪ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበትም አሳስበዋል።