ሚኒስቴሩ በክዋኔ የኦዲት ግኝት መሰረት እያከናወነ ያለው ተግባር ሊሻሻል እንደሚገባ ተመላከተ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ በክዋኔ የኦዲት ግኝት መሰረት እያከናወነ ያለው ተግባር ሊሻሻል እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፡- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በክዋኔ የኦዲት ግኝት መሰረት ክፍተቶቹን ለማስተካከል እያከናወነ ያለው ተግባር ሊሻሻል እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የ2015/16 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር) እንዳሉት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፕሮጀክቶች አፈፃፀም ጋር ተያይዞ ዝቅተኛ አፈፃፀም ማሳየቱን ጠቁመዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመንግስትም ይሁን በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ለሚሰራቸው ለእያንዳንዱ ፕሮጀክቶች የዳሰሳና የአዋጭነት ጥናት አለመስራቱ በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ለታዩ ክፍተቶች መፈጠር ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።
በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዳሰሳና የአዋጭነት ጥናት በመስራት ክፍተቶቹን ማረም እንደሚገባ እና ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም የፕሮጀክቶች መዘግየትና መጓተት ብሎም ቅድሚያ መሰጠት ያለባቸው ፕሮጀክቶችን ቅድሚያ የመስጠት ችግር መኖሩን ጠቁመው፣ በተያዘላቸው ጊዜ ያላለቁ ፕሮጀክቶች ወቅታዊ ሁኔታ የማይታወቅ ሲሆን፣ የፋይናንስና የፊዚካል አፈፃፀማቸው የተስማሚነት ችግር እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ አቋርጦ በጀቱን ወደ ሌላ ፕሮጀክት በማዘዋወር ሂደት ረገድ የህግ፣ የመመሪያ፣ የአሰራር ጥሰት የታየበት በመሆኑ ሊታረም ይገባል ነው ያሉት።
ከሰው ሀብት ጋር ተያይዞም መስሪያ ቤቱ ሰራተኞችን በሪኮመንዴሽን የሚቀጥርበት ሁኔታ ህግና ስርዓት ያልተከተለ በመሆኑ ሰራተኞችን አወዳድሮ ሊቀጥርና አሰራሩ ሊታረም እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከንብረት ማስመለስ ጋር በተያያዘም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የለቀቁና ጡረታ የወጡ ሰራተኞች ያልመለሷቸውን በጥቅል ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የመንግስትና የህዝብ ሀብት በአግባቡ የማስመለስ ስራ መስራት አለበት ብለዋል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው በኦዲት ሪፖርቱ ላይ የቀረበው አፈጻጸም በተወሰኑ ፕሮጀክቶች ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመው፣ ተቋሙ አሁን የሚሰራቸው በርካታ ስራዎች መኖራቸውንና ከዚህ ተነስቶም አጠቃላይ ስራውን ሊፈትሽና ሊያሻሽል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ተጠያቂ የሆኑ አካላትንም በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተጠያቂ አድርጎ ሪፖርት ማድርግ ይገባልም ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋሙ ለሀገር በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን አስታውሰው፣ ከፕሮጀክቶች፣ ከንብረት ማስመለስ፣ ካለአግባብ ከተከፈሉ ክፍያዎች፣ ከሰራተኞች ቅጥር ጋር ተያይዞ በአፈፃፀም ሂደት ጉድለቶች መኖራቸውንና የእርምት እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም ወጪ ወጥቶ ያልተሰሩ ስራዎች ካሉ ፍተሻ እንደሚደረግም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
የፕሮጀክት ውል ሲያዝ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ማወቅና ማማከር ያለበት በመሆኑ በቀጣይ በአግባቡ የሚፈፀም መሆኑን ጠቁመው፣ በአጋር አካላት በተለይ በአለም ባንክ አማካኝነት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ያሉንን ሀገራዊ ስትራቴጂዎችና ንድፎች መሰረት ተደርጎ እንደሚቀረፁ አስረድተዋል።
አገር አቀፍ አንድምታ ያላቸውን ጉዳዮች ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረን ነው የምንፈርመው ያለ እርሱ ይሁንታ አንሰራም ያሉ ሲሆን በተመሳሳይም የፍትህ ሚኒስቴር ይሁንታ የሚያስፈልጋቸው ከሆነም ለሚኒስቴሩ እናሳውቃለን ማለታቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።