በአፍሪካ የህክምና ምርቶችን ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነት የማረጋገጥ አህጉራዊ አቅምን ማጎልበት ይገባል - ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ የህክምና ምርቶችን ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነት የማረጋገጥ አህጉራዊ አቅምን ማጎልበት ይገባል - ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፡- በአፍሪካ የህክምና ምርቶችን ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነት የማረጋገጥ አህጉራዊ አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ።
በአፍሪካ የጤና ዘርፉን እና የህክምና ምርቶችን ጥራትና ደህንነት የማረጋገጥ አቅም ለማሳደግ የአፍሪካ ህብረት ስማርት ሴፍቲ ሰርቪላንስ ፕሮግራም(AU-3S) እ.አ.አ በ2020 ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።
ለ10 ዓመታት የሚተገበረው ይህን ፕሮግራም የሚያስተባብረው ኮሚቴ 6ኛ መደበኛ ስብሰባውን በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
በስብሰባው የተሳተፉት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፥ ፕሮግራሙ በአፍሪካ ጥቅም ላይ የሚውሉ የህክምና ምርቶች ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ጥራት ያላቸውና በህዝቡ የታመኑ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የጋራ አህጉራዊ ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት የስማርት ሴፍቲ ሰርቪላንስ ፕሮግራም አፍሪካ የህክምና ምርቶች ደህንነትና ጥራት በራሷ አቅም እንድታረጋግጥ ትልቅ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮግራሙ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአፍሪካ ህብረት የመድሃኒት ምርቶች ላይ የሚታዩ ስጋቶችን የሚገመግም ኮሚቴ ማቋቋም፣ ብሔራዊ የቁጥጥር ተቋማትን ማጠናከር በድንበሮች ላይ ቅጽበታዊ የቁጥጥር ስራ መረጃዎችን የሚያጋራ ዲጂታል አሰራር መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።
አፍሪካ የህክምና ምርቶችን ጥራትና ደህንነት የማረጋገጥና የቁጥጥር አህጉራዊ አቅሟን እንድታጎለብት በጋራ መስራትና ፕሮግራሙን ማሳካት ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የምግብ እና የመድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ህብረት የስማርት ሴፍቲ ሰርቪላንስ(AU-3S) አፍሪካ ውስጥ ያለውን የመድኃኒት ጥራት፣ ደህንነትና ፈዋሽነት የማረጋገጥ አቅም እያሻሻለ ነው።
እንዲሁም መረጃን የመለዋወጫ ስርዓት በመዘርጋት በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ያለ መርኃ-ግብር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በፕሮግራሙ አማካኝነት መረጃን የማደራጀትና የባለሙያዎችን አቅም በመገንባት በኩል ለውጥ እያመጣች መሆኗን ጠቅሰው፥ በቀጣይም ስኬቶችን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
የአፍሪካ ህብረት የስማርት ሴፍቲ ሰርቪላንስ (AU-3S) ፕሮግራም አስተባባሪ ኬኔት ኦኑ በበኩላቸው ፕሮግራሙ ተግባራዊ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
የተጠናከረ የጥራት ቁጥጥርና ክትትልን ጨምሮ ጠንካራ የጤና ስርዓት በመዘርጋት በኩል የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።
በመድረኩ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የኢትዮጵያ የምግብ እና የመድሃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ፣ የአፍሪካ ህብረት የስማርት ሴፍቲ ሰርቪላንስ (AU-3S) ፕሮግራም አስተባባሪ ኬኔት ኦኑ እና የአባል ሀገራት የብሔራዊ ቁጥጥር ኤጀንሲ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።