ኢትዮጵያ እና ስዊድን የፓርላሜንታዊ ትብብር መፍጠር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ስዊድን የፓርላሜንታዊ ትብብር መፍጠር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፡- በስዊድን እና ስካንዲኒቪያን ሀገራት የኢትዮጵያ አምባሳደር ምህረተአብ ሙሉጌታ ከስዊድን ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ አሮን ኤሚልሰን ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ እና ስዊድን መካከል የፓርላሜንታዊ ግንኙነት መመስረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በስፋት መክረዋል።
ሀገራቱ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ ልማት፣ ሰላምና ደህንነትን ጨምሮ በተለያዩ ቁልፍ የትብብር መስኮች በጋራ መስራት በሚቻልባቸው አማራጮች ላይም ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።
ኢትዮጵያ እና ስዊድን የጋራ ጥቅምን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ መግለጻቸውን በስቶክሆልም የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።
ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ በ1946 መጀመራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።