ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የባንግላዲሽ አምባሳደር አሰናበቱ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የባንግላዲሽ አምባሳደር አሰናበቱ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፡- የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የባንግላዲሽ አምባሳደር ሲክደር ቦዲሩዝማንን አሰናበቱ።
አምባሳደር ሲክደር ቦዲሩዝማን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ እጅግ ደስተኛ እንደነበሩ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ታሪካዊና ቀደምት ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ በቆይታቸው ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይ መሆናቸውንና ሀገሪቱም ለኑሮ ተስማሚና ምቹ መሆኗን ተመልክቻለሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማዕከል ነች ያሉት አምባሳደሩ፤ የአፍሪካ ህብረት መስራች መሆኗን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለቤት መሆኗና የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ባንግላዲሽ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ አቋም እንዳላትም አረጋግጠዋል።
በቆይታቸውም የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ተግባራት ማከናወናቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም በኢኮኖሚና በህዝብ ለህዝብ ትስስርና መሰል ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
በቀጣይም የባንግላዲሽና የኢትዮጵያ ግንኙነት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።