የአምስት ዓመት የፍልሰት የጋራ ስትራቴጂክ ዕቅድና ብሔራዊ ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የአምስት ዓመት የፍልሰት የጋራ ስትራቴጂክ ዕቅድና ብሔራዊ ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፡- የአምስት ዓመት የፍልሰት የጋራ ስትራቴጂክ ዕቅድና ብሔራዊ ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ዛሬ ይፋ ተደርጓል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር ያዘጋጁት የአምስት ዓመት መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል እና መደበኛ ፍልሰትን ለማበረታታት የተዘጋጀ ብሔራዊ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂና የጋራ የአምስት አመት መሪ ዕቅድ ይፋ ተደርጓል።
በመድረኩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር(ዶ/ር) ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የአለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት አመራሮች፣ የተለያዩ ኤምባሲ ተወካዮችና ሌሎች ሃላፊዎቸ ተገኝተዋል።
ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት መንግሥት ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቀረት ብሎም ፍልሰት የሚያመጣቸውን ችግሮች ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በዚህም ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫና የንቅናቄ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀው፤ አሁን ላይ ስትራቴጂዎች ወደ ስራ ሲገባ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ተናግረዋለ።
በዚህም ለአምስት ዓመታት የሚቆየው ብሔራዊ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂና የጋራ የአምስት አመት መሪ ዕቅድ የኢትዮጵያ የፍልሰት አሥተዳደር ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
ስትራተጂክ ዕቅዶቹ የፍልሰት አስተዳደርን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዙ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል እና ለተጎጂዎች ጥበቃና እንክብካቤ መስጠት ያስችላል ብለዋል።
ዕቅዱ የኢትዮጵያ የፍልሰት አሥተዳደርን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ፣ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከልና ለተጎጂዎች ጥበቃና እንክብካቤ ለመስጠት፣ ውጤታማ የተመላሽ ፍልሰተኞች መረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለማሻሻል እና የአቅም ግንባታ ተግባራትን ለማከናወን እንደሚያግዝም ገልጸዋል።
ለዚህም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቢባቱ ዋኔ በበኩላቸው፤ ይፋ የተደረጉት ስትራቴጂክ ዕቅዶቹ መደበኛ የሆነውን በማበረታታትና መደበኛ ያልሆነውን ስደት ለመግታት በቁርጠኝነት መስራት ያስችላል ነው ያሉት።
ህገ-ወጥ ስደትን ለመከላከል በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት መካከል ያለው አጋርነት ወሳኝ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረገው ዕቅዱ ውጤታማ እንዲሆን ድርጅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡