ኢትዮጵያ ዩኤን ሀቢታት ለከተማ ኑሮ እና መሰረተ ልማትን ማሻሻያ ኢኒሼቲቮች ድጋፍ እንዲያደርግ ጠየቀች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዩኤን ሀቢታት ለከተማ ኑሮ እና መሰረተ ልማትን ማሻሻያ ኢኒሼቲቮች ድጋፍ እንዲያደርግ ጠየቀች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፦ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ሰፈራ መርሃ-ግብር (ዩኤን ሀቢታት) የከተማ ኑሮ እና መሰረተ ልማትን የሚያሻሽሉ ኢኒሼቲቮችን እንዲደግፍ የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን ጥሪ አቀረቡ።
በከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን የተመራ ከፍተኛ የመንግስት ልዑክ በኬንያ እየተካሄደ ባለው የመጀመሪያው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ሰፈራ መርሃ-ግብር (ዩኤን ሀቢታት) የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ስብስባ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
የቦርድ ስብስባው ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።
በስብሰባው ላይ ዩኤን ሀቢታት በኢትዮጵያ እና በሌሎች ሀገራት እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ ሪፖርት አቅርቧል።
በሪፖርቱ ኢትዮጵያ በከተማ ልማት እያከናወነች ያለው ስራ ከፍተኛ አድናቆት ማግኘቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያም የከተማ ልማት የስኬት ተሞክሮዎቿን አቅርባለች።
የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን ኢትዮጵያ በዩኤን ሀቢታት የሚደገፉ እንዲሁም ከብሄራዊ የከተማ ልማት ፖሊሳዊ እና የ10 ዓመት የልማት እቅዷ ጋር የተናበቡ ፕሮጀክቶቿን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
ዩኤን ሀቢታት የከተማ ኑሮ ሁኔታ እና መሰረተ ልማት ማሻሻያ ኢኒሺዬቲቮችን በተጠናከረ መልኩ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ሚኒስትር ዴኤታው ከእ.አ.አ 2026 እስከ 2029 ለመተግበር ያዘጋጀው ረቂቅ የስትራቴጂክ ፕላን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የቤቶች አቅርቦት ፈተናዎችን በግልጽ ያስቀመጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የማይበገር የከተማ የቤት ልማት አሰራርን ለመተግበር ቁርጠኛ እንደሆነችም ገልጸዋል።