ኢትዮጵያ እና ኬንያ አንድ አለቅ የድንበር ጣቢያዎች ማስፋፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን እና የኬንያ ገቢዎች ባለስልጣን የአንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት ጣቢያዎችን/One Stop Border Posts/ ማስፋፋት እና በሌሎች የጉምሩክ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ውይይት ተደርጓል፡፡

በውይይቱ የሁለቱ ሀገራት ሌሎች ባለድርሻ ተቋማትም መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡


 

በውይይቱ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፣ በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደር ጆርጅ አሪና፣ የዓለም ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ መስሪያ ቤቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

የጉምሩክ አስተዳደሮች ንግድን የማሳለጥ እና የድንበር ቁጥጥር ስርዓትን የማጠናከር ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የጉምሩክ ተቋማት ይህን ሚናቸውን ለመወጣት ከአቻ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበው ኮሚሽኑ ከኬንያ ገቢዎች ባለስልጣን ጋር በትብብር እየሰራ ያለውን ስራ ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ከዓመታት በፊት አገልግሎት መስጠት የጀመረው በኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር የሚገኘው የሞያሌ አንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት ማዕከል ተደጋጋሚ ፍተሻዎችን በማስቀረት የተፋጠነ የጉምሩክ አገልግሎት እንዲኖር ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ውህደት በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እና በሌሎች አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ብሎኮች አማካኝነት እየተፋጠነ መሆኑን ገልጸው ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ በዚህ ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚናዋን እንድትወጣ የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደር ጆርጅ አሪና በበኩላቸው፤ በኬንያና በኢትዮጵያ ድንበር ላይ የአንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት ማዕከል መገንባት የሁለቱን ሀገራት እድገት ለማፋጠን ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ ተጨማሪ የጋራ አንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን ሱፍቱ እና ራሙ በሚባሉ የድንበር አካባቢዎች መገንባት ስለሚቻልበት ሁኔታ ብሎም በሁለቱ ሀገራት መካከል የንግድ እና የህዝብ- ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር ዓለማ ያደረገ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ሁለቱ ተቋማት ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችል የትብብር ስምምነት ለመፈራረም የሰነድ ዝግጅት በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

የአንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት(One stop border post) በአጎራባች ሀገሮች ድንበር ላይ በጋራ የሚገነቡና የድንበር ቁጥጥር የሚያደርጉ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በአንድ ቦታ እንዲገኙ በማድረግ ተደጋጋሚ ፍተሻዎችን በማስቀረት የሸቀጦችንና የሰዎችን እንቅስቃሴን ለማፋጠን የሚረዱ ማዕከላት ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ እና በኬንያ ድንበር የተገነባው የሞያሌ አንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ህዳር 30 ቀን 2013 ዓ.ም ተመርቆ ስራ መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም