የሶስት ከተሞች የመካከለኛ መስመር ግንባታ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዊልኪንስ ኢንጅነሪንግ ኩባንያ ከተሰኘ ድርጅት ጋር የሶስት ከተሞች የመካከለኛ መስመር ግንባታ ስምምነት ተፈርሟል።

ስምምነቱ አገልግሎቱ በቀጣይ ለመገንባት በዕቅድ ከያዛቸው የ10 ከተሞች የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ማሻሻያና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት አካል የሆኑት የደበረብርሃን፣ ሱሉልታ እና ቢሾፍቱ ከተሞች የመካከለኛ መስመር የመልሶ ግንባታና ማሻሻያ ፕሮጀክትን የተመለከተ ነው፡፡

የፕሮጀክት ግንባታ ስምምነቱ የተከናወነው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና በጋናው ዊልኪንስ ኢንጅነሪንግ ኩባንያ መካከል ነው፡፡

በስምምነቱ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ጌቱ ገረመው(ኢ/ር) እንዳሉት ፕሮጀክቱ በከተሞቹ ያለውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት አስተማማኝ በማድረግ ደንበኞች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብና የጥራት ደረጃ መጠናቀቅ እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የዊልኪንስ ኢንጅነሪንግ ኩባንያ ተወካይ ኦማን ፍሪምፖንግ በበኩላቸው ፕሮጀክቱን በተያዘው ጊዜና የጥራት ደረጃ አጠናቀሙ እንደሚያስረክቡ ገልፀዋል፡፡

የመልሶ ግንባታ ስራው 386 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር የሚሸፍን የመልሶ ግንባታ እና 315 ኪሎ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው 87 አዲስ ትራንስፎርመሮች እንደሚተከሉም ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የኤሌክትሪክ የመቆራረጥ ድግግሞሹን 45 በመቶ እና የቆይታ ጊዜውንም በ50 በመቶ እንደሚቀንስ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም የእንጨት ምሶሶዎችን ወደ ኮንክሪት መቀየር፣ ያልተሸፈኑ የኤሌክትሪክ መስመርን በተሸፈኑ ገመዶች የመቀየር ስራ እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡

ፕሮጀክቱ የሚከናወነው ከአለም ባንክ በተገኘ 17 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ብድር ሲሆን ግንባታውም በሁለት አመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም