ረቂቅ አዋጁ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሥርዓትን የሚያዘምን ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፦ ረቂቅ አዋጁ የተቀናጀና ዘላቂነት ያለው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ሥርዓትን ለማዘመን እንደሚያግዝ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ ተናገሩ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም ባካሄደው 10ኛ መደበኛ ስብሰባው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ የማሻሻያ ረቂቅ ላይ ተወያይቶ ለውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና የአካባቢ ልማት እንዲሁም ለከተማ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴዎች መምራቱ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም ሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች እና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በረቂቅ አዋጁ ላይ ዛሬ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት መድረክ አካሂደዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ አረንጓዴ፣ ውብና ፅዱ ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍና ለአካባቢ ምቹ መደላድል የሚፈጥር ሕግ አስፈላጊ እንደሆነም ገልጸዋል።

ነባሩ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ ቁጥር 513/1999 አሁን ካለው የሀገሪቱ ዕድገት አንጻር ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚመነጨው የቆሻሻ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ በነባሩ አዋጅ መምራት ባለመቻሉም አዲስ አዋጅ ማዘጋጀት ማስፈለጉን ጠቁመዋል።

አግባብነት የሌለው የቆሻሻ አወጋገድ ለአፈር፣ ለውሃ፣ ለአካባቢ እና ለአየር ንብረት ብክለት እንደሚያጋልጥ ጠቅሰው፥ ቆሻሻውን ከምንጩ ለመቀነስና የአያያዝና የአወጋገድ ስርዓቱን ማሻሻል አስፈላጊ እንደሆነም አንስተዋል።

ደረቅ ቆሻሻ በአካባቢ ሥነ-ምህዳር እና በሰዎች ደኅንነትና ጤና ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑ ይህን በሕግ ምላሽ ለመስጠት አዋጁ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ፕላስቲክ ማምረት፣ ለገበያ ማቅረብ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት፣ መሸጥ፣ ማከማቸት ወይም መጠቀም በረቂቅ አዋጁ የተከለከለ መሆኑን ተናግረዋል።

የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ሲተገበር በሀገሪቱ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጣም ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የተለያዩ የተቋማት ተወካዮች በበኩላቸው የአካባቢ ጥበቃና ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ የሁሉም ድርሻ በመሆኑ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ፕላስቲክና ጎማ አምራቾች ማህበር ፕሬዝዳንት ምንተስኖት ለማ የአካባቢ ጥበቃ የሁላችን ጉዳይ ነው፤ ነገር ግን አንዳንድ በረቂቅ አዋጁ የተካተቱ ድንጋጌዎች በአምራቾች ላይ ጫና የማያሳድሩ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

የውሃ፣መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈትያ አህመድ ረቂቅ አዋጁ ለአካባቢ ጥበቃ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፤ ከህዝብ የቀረቡ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ለረቂቅ አዋጁ ተጨማሪ ግብዓት ይሆናሉ ብለዋል።

የከተማ፣ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን(ዶ/ር) በበኩላቸው ሀገር ያለችበትን የኢኮኖሚ እድገትና የከተሞች መስፋፋት እንዲሁም የማኅበረሰብ ዕድገት ማዕከል ያደረገ የቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ አስፈላጊ ግብዓቶችን በመሰብሰብ ጠንካራ አዋጅ ማዘጋጀት ይቻል ዘንድ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት መድረኩ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም