ግብርናውን በመካናይዜሽን በመደገፍ ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ግብርናውን በመካናይዜሽን በመደገፍ ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል

ባህርዳር፣ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፡- በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እየተመዘገበ ያለውን እድገት ለማስቀጠል በመካናይዜሽን የተደገፈ እንዲሆን ትኩረት መደረጉን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) ገለጹ።
አዲሱን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የሚያስተዋወቅ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።
ሚኒስትር ዴኤታው መለስ መኮንን (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ምርታማነት እንዲኖር የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲው መሻሻሉን ገልጸዋል።
ፖሊሲው በአለም ላይ ያለውን የተሻለውን የአመራረት ዘይቤ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የዘርፉን መልካም አጋጣሚዎችና የመልማት አቅምን አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የተሻሻለው የግብርና ፖሊሲም ቀጣይነት ያለው የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የምግብ ሉአላዊነትን ማረጋገጥ፣ ሀገራዊ ምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን ማጎልበት ላይ ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል።
ለዚህም የግብርና መካናይዜሽንና አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ግብአትና ለወጭ ንግድ በቂ ምርት ወጥ በሆነ መልኩ ማምረት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በሰብል፣ በእንስሳት፣ በደንና ሌሎች የግብርና ዘርፎች ተወዳዳሪነት በማረጋገጥ በአገር ደረጃ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት በሚሰራው ስራ አጋዥ ሚና የሚጫወት ነው ብለዋል።
ለፖሊሲው ተፈጻሚነት በየደረጃው ያለው አመራር፣ ባለሙያውና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መረባረብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በበኩላቸው የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጅ የተደገፈ አሰራር መተግበር ይገባል ብለዋል።
በዚህም ለገበያና ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆን ምርት ላይ በማተኮር ለመረባረብ የፖሊሲው መሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው የክልሉ መንግስት ለተግባራዊነቱ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ የገጠር ዘርፍ አሰተባባሪና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንደገለጹት በክልል ደረጃ ዛሬ የተጀመረው ፖሊሲውን የማስተዋወቅ ስራ እሰከ ታች ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ፖሊሲውን መሰረት በማድረግም ለባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች አጋር አካላት የግንዛቤ ፈጠራ ስራ በቀጣይነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የዘርፉ አመራሮች ተገኝተዋል።