በኦሮሚያ ክልል በአዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ

ጭሮ፣ ጅማ፣ ነቀምቴ መጋቢት 17/2017 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በአዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን የተለያዩ አካባቢ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የኦሮሚያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት አዲስ የቀበሌ አደረጃጀት ዘርግቶ ህዝቡ በአቅራቢያ የተሻለ የመንግስት አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ማድረጉ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ እና ምላሽ በሰጡበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል የተደራጁ የቀበሌ መዋቅሮች ለተሻለ አገልግሎት እየተጠናከሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢዜአ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ፣ ጅማ እና ምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ በአዲስ መልክ የተዋቀሩ የቀበሌ መዋቅሮች እየሰጡ ያሉትን አገልግሎት በተመለከተ ቅኝት አድርጓል።

በዚህም ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የጭሮ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት ከዚህ ቀደም እስከ ሁለት ቀን ወደ ወረዳ ማእከል በመመላለስ ሲያገኙ የነበረውን አገልግሎት በቀበሌ ደረጃ በሰአታት ውስጥ እያገኙ ነው፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡን መካከል የጨፌ አራራ ቀበሌ ነዋሪና የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ሀረገወይን ተገኔ አንዷ ሲሆኑ ለመኖርያ ቤት እድሳት ወደ ቀበሌ መምጣታቸውን ገልፀው ጉዳያቸው በሰዓታት ውስጥ እንደተፈጸመላቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ለመኖሪያ ቤት  እድሳት ወደ ከተማው አስተዳደር በመመላለስ ከሁለትና ሶስት ቀናት በላይ እንደሚያጠፉም ነው የተናገሩት።

በመሬት ይዞታ ልኬትና በወሰን ማስተካከል ጉዳይ በቀበሌ ደረጃ አገልግሎት እንዳገኙ የተናገሩት ወይዘሮ ውባለም መንግስቱ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም በከተማ አስተዳደር ደረጃ አገልግሎቱ ሲሰጥ ለቀናት የመመላለስ ችግር ነበር ያሉት አስተያየት ሰጪዋ  ''ይህም ጊዜያችንን ሲያባክንብን ነበር'' ብለዋል፡፡

በጅማ ዞንም በተመሳሳይ በቀበሌ ደረጃ የተዋቀሩ አደረጃጀቶች ህዝቡን በቅርበት እያገለገሉ መሆኑን ተገልጋዮች ተናግረዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል በዞኑ የናዳ ወረዳ የመረዋ ቀበሌ ነዋሪ አባ ጀበል አባ ወሊ፤ ''የቀበሌ አደረጃጀቱ ለችግሮቻችን መፍትሔ ለመስጠት እና የተለያዩ አገልግሎቶችን እንድናገኝ አግዞናል'' ብለዋል።

በተለይም የቀበሌ አደረጃጀቱን ተከትሎ የተለያዩ የመሰረተ ልማቶች እየተስፋፉ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አስረድተዋል።

ሌላው ነዋሪ አባ ረሻድ አባ ቢያ በበኩላቸው ከዚህ በፊት አገልግሎት ለማግኘት ወረዳ ማእከል ድረስ በመሄድ የትራንስፖርት ወጪና  የድካም እና እንግልት ሲደርስባቸው እንደቆየ አንስተዋል።

በተመሳሳይ አዲስ የተዘረጋው የቀበሌ አደረጃጀት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ያሳለጠ እና ተጠቃሚ ያደረጋቸው መሆኑን የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ  ወይዘሮ ስኳሬ ቀጄላ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በቀበሌ ደረጃ በተዘረጋው የአገልግሎት አሰጣጥ ያለ እንግልት በመገልገል ላይ እንደሚገኙ  ገልፀዋል።

የቀበሌ መዋቅሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰቡ ክፍሎች ትኩረት ማግኘት መቻላቸውን በማንሳት በተለይ ዜጎች በመደራጀት ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ፣ የመኖሪያ ቤት እንዲያገኙ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አንስተዋል።

ሌላኛዋ የከተማዉ ነዋሪ ወይዘሮ ለሊሴ ነጋሳ ከዚህ በፊት መታወቂያ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደነበረ ጠቅሰው ዛሬ ላይ ግን የሚያስፈልገውን ሂደት በሟሟላት ብቻ ነዋሪዎች የሚፈልጉትን እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

በነቀምቴ ከተማ የቡርቃ ጃቶ ቀበሌ አስተዳደሪ አቶ መልካሙ ቡልቲ፤ በቀበሌ መዋቅሩ የተገልጋዩን እንግልት ለመቀነስ የእረፍት ቀናትን ጨምሮ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

መዋቅሩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ማሻሻል፣ በኢንቨስትመንት ተይዘው ለረዥም አመታት ያልለሙ ቦታዎችን ለወጣቶች በማስረከብ፣ የህብረተሰቡን ጥያቄዎች በቅርበት በመረዳት እና ያለአግባብ የሆኑ ወጪዎችን በመቀነስ ዘርፍ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።


 

የጭሮ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጀማል ጎሳዬ አንዳሉት በአዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት በከተማው የሚገኙ አስሩም ቀበሌዎች ከ100 በላይ አዳዲስ  ባለሙያዎች ለህብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት እንዲሰጡ ተመድበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በአመቱ አገልግሎቱን ለማጠናከር  ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሁለት የቀበሌ ፅህፈት ቤቶች ግንባታ እያከናወነ መሆኑን ገልጸው ሁሉንም የቀበሌ ጽህፈት ቤቶች በቁሳቁስ በማሟላት ለህብረተሰቡ ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም ነው አቶ ጀማል የተናገሩት፡፡


 

የጅማ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ የሱፍ ሻሮ፤ በዞኑ ህዝቡ በቀበሌ ደረጃ አስፈላጊ አገልግሎት መጠቀም እንዲችል በሁሉም ቀበሌዎች መዋቅር እየተዘረጋ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ 562ቱ ቀበሌዎች አደረጃጀቱ በትኩረት እየተተገበረ ሲሆን ህዝቡም ጥሩ ግብረ መልስ እየሰጠ መሆኑን አመልክተው ለሁሉም ቀበሌዎች የአስተዳደር ባለሙያዎች ተመድበው ስራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም