የሸገር ከተማ በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት ከሁለት ሺህ በላይ ባለሀብቶችን ለመቀበል ተዘጋጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
የሸገር ከተማ በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት ከሁለት ሺህ በላይ ባለሀብቶችን ለመቀበል ተዘጋጅቷል

ሸገር፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፦ የሸገር ከተማ አስተዳደር በተያዘው በጀት ዓመት ቀሪ ጊዜ ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ ባለሀብቶችን ለመቀበል መዘጋጀቱን የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ጉዮ ገልገሎ ገለፁ።
ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት የተውጣጡ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራርና ባለሙያዎች በሸገር ከተማ የተለያዩ የልማት ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።
ምክትል ከንቲባው በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ሸገር ከኢንቨስትመንት አንጻር ምቹ ሁኔታዎችን ያሟላ ከተማ ነው።
አስተዳደሩ ይህን መልካም እድል በመጠቀም ከመሠረተ ልማት ጀምሮ ኢንቨስትመንትን ለማፋጠን የሚያግዙ በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።
በከተማ አስተዳደሩ እስካሁን ከ4 ሺህ 500 በላይ ባለሀብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን፤ ብዙዎቹም በሚፈለገው መንገድ ምርት እያመረቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም የከተማውን የኢንቨስትመንት ምርታማነት ከ42 በመቶ ወደ 54 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ተናግረው፤ በበጀት ዓመቱ መጨረሻም ምርታማነቱን ወደ 65 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራትም ከ2 ሺህ 200 በላይ ባለሀብቶችን ለመቀበል ዝግጅት መደረጉን ተናግረው ለዚህ ሥራም ከ3 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የኢንቨስትመንት ስራውም ወደ ሥራ ሲገባ ከ700 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ብለዋል።
የሸገር ከተማ ከመመስረቷ በፊት አርሶ አደሮች በኢንቨስትመንት ምክንያት በቂ ካሳ ሳይከፈላቸው ከመኖሪያ ቤታቸው ሲፈናቀሉ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ባለው የኢንቨስትመንት ስራ ግን ለከተማው ማህበረሰብና ለአርሶ አደሩ ቅድሚያ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ከባለሀብቶቹ መካከል አቶ ታዲዮስ ጌታቸው፣ ከተማ አስተዳሩ ለባለሀብቶች እያደረገ ያለው ድጋፍ በጎ መሆኑን አንስተው ይህም መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።
ሌላው ባለሃብት አቶ በላይነህ ክንዴም የኢንቨስትመንት ስራዎቹ የቴክኖሎጂ ሽግግር እያደረጉ መሆኑንና የውጭ ምንዛሪ ወጪን በመቀነስ ለብዙ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻላቸውን አስረድተዋል።