ቀጥታ፡

በማህበር ተደራጅተን የተሻሻለ የአቮካዶ ችግኝ እያባዛን ለገበያ በማቅረብ ውጤታማ ሆነናል - ወጣቶች

ዲላ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፡- በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በማህበር ተደራጅተው የተሻሻለ የአቮካዶ ችግኝ እያባዙ ለገበያ በማቅረብ ውጤታማ መሆናቸውን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ወጣቶች ተናገሩ።

በዞኑ የተደራጁ አምስት የወጣት ማህበራት በየዓመቱ ከ200ሺህ በላይ የተሻሻለ የአቮካዶ ችግኝ በማባዛት እያሰራጩ እንደሚገኙ ተመልክቷል።


 

ወጣት ዮሴፍ ጥላሁን በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ "ወልጋርጋሮ" የተሻሻለ የአቮካዶ ችግኝ ብዜት ማህበር ሰብሳቢ ሲሆን፤ ማህበራቸው የዛሬ አራት ዓመት በተሻሻለ የአቮካዶ ችግኝ ብዜት ላይ በአስር አባላት ወደ ስራ መግባቱን ለኢዜአ ገልጿል።

በየዓመቱ በአማካይ ከ10ሺህ በላይ የተሻሻለ የአቮካዶ ዝሪያ ያለው ችግኝ በማባዛት ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ እያሰራጩ መሆኑን ጠቅሶ፤ ከዚህም በምናገኘው ገቢ ውጤታማ ሆነናል ብሏል።

ይህም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እንደሆነ ጠቅሶ፤ ለዘንድሮ የሚተከል ከ20 ሺህ በላይ የተሻሻለ የአቮካዶ ችግኝ እያዘጋጁ መሆኑንና ከሽያጩ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ማቀዳቸውን አብራርቷል።  


 

ሌላው በዞኑ "የዳናነ" የአቮካዶ ችግኝ ብዜት ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ብርሃኑ ከበደ በበኩሉ፤ ሥራው የሙያ ባለቤት እንዳደረጋቸው ጠቅሶ መንግስት መነሻ ካፒታል፣  የሥራ ቦታና ዝሪያዎችን የማዳቀል ክህሎት እንድንጨብጥ ስልጠና ሰጥቶናል ብሏል።

በሚያገኙት ገቢና ክህሎት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ በመሆን ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውን እየረዱ እንደሚገኙ ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ከ10ሺህ በላይ የተሻሻለ የአቮካዶ ችግኝ አባዝተው ለተከላ ማዘጋጀታቸውንና ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እናገኛለን ብለው እንደሚጠብቁ ተናግሯል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለፍራፍሬ ልማት ትኩረት መስጠቱ የገበያ እድል ፈጥሮልናል ብሏል።


 

በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ሲሳይ ታቦር፤ ከአራት ዓመታት በፊት የተሻሻለ የአቮካዶ ዝሪያ ከማህበራት ተረክበው በማልማት ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ያላቸው ከ200 በላይ የአቮካዶ ዛፎች ምርት መስጠት መጀመራቸውን ተከትሎ በአቅራቢያቸው ከሚገኘው የዲላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ምርታቸውን እያቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በክልሉ ግብርና ቢሮ የዘላቂ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ኢዮብ ሳሊ በበኩላቸው፤ በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለፍራፍሬ ልማት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተሻሻለ የአቮካዶ ችግኝ ብዜት ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰው፤  ለአረንጓዴ አሻራ የፍራፍሬ ችግኝ አቅርቦት ምንጭ እንደሆኑም አስረድተዋል።


 

ለአብነትም በጌዴኦ ዞን አምስት የወጣት ማህበራት በየዓመቱ ከ200ሺህ በላይ የተሻሻለ የአቮካዶ ችግኝ በማባዛት እያሰራጩ እንድሚገኙ አመልክተዋል።

አርሶ አደሩ ችግኙን ተጠቅሞ በማልማት ምርቱን ለኢንዱስትሪ ፓርኮች በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን የገበያ ትስስር መፈጠሩንም ገልጸዋል።

ከክልሉ ግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለተከላ እየተዘጋጀ ካለው ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ችግኝ መካከል ከ20 በመቶው የሚበልጠው የፍራፍሬ ዝርያ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም