ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተሟላ ትግበራ የመንግስትን ጥረት በማገዝ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም መገንባት ይገባል

መቀሌ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፦ ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተሟላ ትግበራ የፌዴራል መንግስትን ጥረት በማገዝ በትግራይ ክልል ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም መገንባት እንደሚገባ ተገለጸ።

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት በፕሪቶሪያ በተደረሰው የሰላም ስምምነት እልባት በማግኘቱ በክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰላምና መረጋጋት መፈጠሩ ይታወቃል።

ከሰላምና መረጋጋት ባለፈም በክልሉ ተቋርጠው የነበሩ የማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲመለሱ በማድረግ የፌዴራሉ መንግስት ተጨባጭ ስራዎች የተስተዋሉበትም ነው።

በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ሲሰራና በስምምነቱ መሰረትም የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።

በክልሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው ለሀገር መከላከያ በማስረከብ በተሃድሶ ኮሚሽን በኩል ስልጠና ወስደው በዘላቂነት ማቋቋም እንደሚገባም ስምምነቱ ያስገድዳል።

ይሁን እንጂ የትጥቅ ማስፈታት ሂደቱ እስካሁን በሚፈለገው ልክ አለመከናወኑ ለሰላም ሂደቱ እንከን የሚፈጥር መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናግረዋል።

በመሆኑም ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተሟላ ትግበራ የመንግስትን ጥረት በማገዝ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም መገንባት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የእንስሳት ህክምና ኮሌጅ ዲን አብርሃም ብስራት(ዶ/ር)፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በተለይም ለክልሉ ህዝብ የሰላም መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የሰላም ስምምነቱን ለመተግበር የፌዴራል መንግስት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀው ሌሎችም የድርሻቸውን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የስምምነቱን ሂደት መተግበር ከምንም በላይ ለትግራይ ክልል ህዝብ ዘላቂ ሰላምና ልማት መሰረት የሚያኖር መሆኑን አንስተው የሰላም ጉዳይ ለሁሉ ነገር ወሳኝ በመሆኑ ለዚሁ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በክልሉ ጦርነትን ከማስቆምም ባለፈ በወቅቱ የነበሩትን ውስብስብ ችግሮች መፍታት ያስቻለ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሳካት የፌዴራል መንግስትን ጥረት በማገዝ በክልሉ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም መገንባት ይገባል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ ዮሃንስ ተኽለ (ዶ/ር)፤ ከምንም በላይ ለሰላም የሚከፈል ዋጋ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ዘላቂ እንዲሆን የመንግስት ጥረት እንዳለ ሆኖ የልሂቃን፣ ምሁራን፣ የሲቪክ ማህበራት እና አጠቃላይ የህዝቡ ጥረትና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የድህረ ምረቃ አስተባባሪ ንጉስ አበበ(ዶ/ር)፤ የሰላም ጉዳይ የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ለቀጣይነቱ በጋራ መስራት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት የፌዴራሉ መንግስት ያደረገውን ጉልህ አስተዋጽኦ አድንቀዋል።

የትግራይ ክልል ህዝብ ሰላምን፣ ልማትንና መረጋጋትን እንደሚሻ አንስተው፤ የግጭት አባዜ ያለበትን ቡድን ህዝቡ መታገልና አደብ ማስገዛት አለበት ማለታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም