የማዕድን ዘርፍ የፖሊሲ እና የአሰራር ማዕቀፎች የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ያማከሉ መሆን ይኖርባቸዋል- ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የማዕድን ዘርፍ የፖሊሲ እና የአሰራር ማዕቀፎች የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ያማከሉ መሆን ይኖርባቸዋል- ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር)
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፦ የማዕድን ዘርፍ የፖሊሲ እና የአሰራር ማዕቀፎች የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ያማከሉ መሆን እንደሚገባቸው የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ(ኢ/ር) ገለጹ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ የሚመራበትን የሕግ ማዕቀፍ ረቂቅ የማዘጋጀትና ሌሎች ኃላፊነቶችን ለመወጣት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ከወራት በፊት ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።
ሁለቱ ተቋማት የዚሁ ስምምነት አካል የሆነውን የማዕድን ሃብት አስተዳደር ፖሊሲን፤ አዋጅና ደንብ መከለስ የሚያስችል የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ዛሬ አካሂደዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ሃብታሙ ተገኝ(ኢ/ር) በመድረኩ እንዳሉት የሚቀረጹ ፖሊሲዎችና የሚረቀቁ ሕጎች የማኅበረሰብ ተጠቃሚነትና ለዘርፉ ልማት ጠቀሜታ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል።
የማዕድን ውጤቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ያላቸውን ተፈላጊነት ያማከለ ጠንካራ አጋርነትና ትብብር መፍጠርን ግምት ውስጥ ያስገቡ መሆን አለባቸው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር ) በበኩላቸው፤ መንግስት ለማዕድን ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ከግምት ያስገባ የሕግ ማዕቀፍ፣ የፖሊሲ ክለሳና የማዕድን ግብይትና የፔትሮሊየም ረቂቅ አዋጅ ዝግጅቶች በዩኒቨርሲቲው በኩል እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።
የረቂቅ ፖሊሲውና የአዋጆቹ ዝግጅት ሲጠናቀቅ፣ ሌሎች የህግ ማዕቀፎችን የማርቀቅ ስራ እንደሚቀጥል ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በተጨማሪም የዲጂታል ልማት እቅድ ዝግጅት በተያዘው ዓመት እንደሚጀመርም ተጠቁሟል።