የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና ሩሲያ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና ሩሲያ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
አምባሳደር ኢቭጌኒ ከሩሲያ መንግስት የተላከ የመልካም ምኞት መግለጫ ያደረሱ ሲሆን ሊቀመንበር ሆነው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታም ገልጸዋል።
ውይይቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና ሩሲያ ያላቸውን ጠንካራ አጋርነት አመላካች መሆኑን ህብረቱ በመረጃው አመልክቷል።
ሁለቱ ወገኖች በአፍሪካ መር የሰላም እና ደህንነት ኢኒሼቲቮች፣ የማህበረሰብ ጤና፣ ኢኮኖሚ እና ግብርና ልማት ላይ ያላቸውን ትስስር ማጠናከር የሚኖረውን የጎላ ፋይዳም አንስተዋል።
የጋራ ፍላጎትን ማዕከል ባደረገ መልኩ የግንኙነት መስኮችን መለየት እና ያሉትን የትብብር መስኮች ማጠናከር የሚያስችል ቋሚ የከፍተኛ ምክክር አማራጭ መፍጠር እንደሚገባም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።