በድሬዳዋ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ድሬዳዋ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፡- በድሬዳዋ አስተዳደር የነዋሪዎችን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሰይፉ ታደሰ(ዶ/ር) ተናገሩ።

በድሬዳዋ የብልጽግና ፓርቲ አባላት ዛሬ በለውጡ ዓመታት የተገኙ ውጤቶችን ማስቀጠል የሚያስችል ውይይት አካሂደዋል።


 

ውይይቱን የመሩት የከንቲባው የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሰይፉ ታደሰ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካው ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በየተቋማቱ ዲጂታል አሰራሮችን በመዘርጋት ለህብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ተደርገው የህዝብ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እየተመለሱ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል።

እየተመዘገቡ ለሚገኙ የለውጥ ውጤቶችም የብልጽግና ፓርቲ አባላት ግንባር ቀደም ተሳትፎ ወሳኝ አበርክቶ እንዳለውም ተናግረዋል።

እነዚህን የለውጥ ውጤቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አባላቱ እያደረጉ የሚገኙትን ርብርብ አጠናክረው እንዲቀጥሉም አስገንዝበዋል።

የአስተዳደሩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀ በበኩላቸው አሰባሳቢ የጋራ ትርክቶችንና የጋራ ማንነትን በማነፅ በኩል ነዋሪው በየመስኩ የሚያደርገው ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ፈጣንና ትክክለኛ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ይበልጥ እንዲጎለብቱ ትኩረት መሰጠቱን በመግለፅ።

የተጀመሩትን የልማት ስራዎች በቅንጅት ማሳካት የድሬዳዋን ከፍታ ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ካሊድ አህመድ ናቸው።

ከተረጂነት ወደ አምራችነት እየተደረገ የሚገኘውን ጉዞ ለማፋጠን የብልጽግና ፓርቲ አባላት ከመቼውም ጊዜ በላይ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም