ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በዲጂታላይዜሽን እና በቴክኖሎጂ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለዓለም ማስተዋወቅና ትስስር መፍጠር ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ በዲጂታላይዜሽን እና በቴክኖሎጂ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለዓለም ማስተዋወቅና ትስስር መፍጠር ያስችላል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017(ኢዜአ)፡- ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 በኢትዮጵያ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና በቴክኖሎጂ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለዓለም የሚያስተዋውቅ እና ትስስር የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) በጋራ የሚያዘጋጁትን ኤክስፖ በተመለከተ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ እንደገለጹት፤ ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 ከግንቦት 8 ቀን ጀምሮ ለሶስት ቀናት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ይካሄዳል፡፡
ኤክስፖው ኢትዮጵያ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ያስመዘገበቻቸው ስኬቶችን እና በዲጂታል ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ኤክስፖው የሳይበር ደህንነት፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የፋይናንስ ደህንነት፣ ስማርት ሲቲ እና የቴክኖሎጂ ትምህርት ትኩረት የሚያደርግባቸው መስኮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ከ10 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች፣ ከ100 በላይ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንዲሁም ከ50 በላይ ስታርታፖች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ኤክስፖው ከ20 በላይ ጥናቶች፣ የፓናል ውይይቶች እንዲሁም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሮቦቲክስ ውድድሮች የሚካሄዱበት መድረክ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ስለሆነም በኢትዮጵያ የተሰናዳው ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 በተሳታፊም ሆነ በትኩረት መስኩ የምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የቴክኖሎጂ ሁነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኤክስፖው ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በሌሎች የቴክኖሎጂ መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶቿን ለዓለም የምታስተዋውቅበት፣ ከሌሎች ልምድ የምትቀስምበትና ትስስር የምትፈጥርበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት ከቅንጦት ይልቅ በሽታን በመከላከል፣ ትምህርትን በማስፋፋትና ድህነትን በመቀነስ ለሰው ልጅ መሰረታዊ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ከድህነት ለመውጣት ለሚደረገው ጥረት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡
በተለይም የግሉ የቴክኖሎጂ ተዋንያን በስፋት እንዲሳተፉ በማድረግ በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች ልምድ የሚለዋወጡበትን አውድ ይፈጠራል ብለዋል።