ቀጥታ፡

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቀን ከ14 ሺህኪሎ ግራም በላይ የአሳ ምርት የሚገኝበት አቅም ተፈጥሯል- ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤መጋቢት 17/2017 (ኢዜአ)፦ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቀን ከ14 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የአሳ ምርት የሚገኝበት አቅም መፈጠሩን በግብርና ሚኒስቴር አሳ ሀብት ልማት ዴስክ ሃላፊ ዶክተር ፋሲል ዳዊት ገለጹ።

በግብርና ሚኒስቴር አሳ ሀብት ልማት ዴስክ ሃላፊ ዶክተር ፋሲል ዳዊት ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ እምቅ የአሳ ሀብት ቢኖራትም በተለያዩ ተግዳሮቶች ምክንያት በዘርፉ ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች፡፡

በሀገር ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአሳ ልማት ዘርፍ ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶችን በመፍታት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በዚህም በአሳ ምርታማነት ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን አንስተው፥ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውስጥ የአሳ ሀብት ልማት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በግድቡ በስፋት ተፈላጊ የሆኑ የአሳ ዝርያዎች እየተመረቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም በቀን ከ14 ሺህኪሎ ግራም በላይ የአሳ ምርት የሚገኝበት አቅም መፈጠሩን አብራርተዋል።

በህዳሴ ግድብ ውስጥ የተለያዩ የአሳ ዝርያዎች መኖራቸውን የገለጹት ዶክተር ፋሲል የሚመረተው አሳ ተፈላጊነት ከፍተኛ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

ዘርፉ ካላው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባለፈ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

እንደ ሀላፊው ገለጻ፥ በቀጣይ የአሳ ምርትን የበለጠ ለማሳደግ የአሳ ጫጩቶችን ማሰራጨት እና አሳ በሌለባቸው የውሀ አካላት ላይ አሳ የሚመረትባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ የዓሳ ሀብት ባለሙያ አቶ ቡሸን ፉፋ በበኩላቸው፥ የህዳሴ ግድቡ በክልሉ የአሳ ምርት መመረቱ የክልሉን ብሎም የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል ከፍተኛ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

በዘርፉ 64 ማህበራት መደራጀታቸውንና ከእነዚህ ውስጥ 23 ማህበራቶች የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስታውቀዋል ።

በቀጣይም ወደ ስራ ያልገቡ ማህበራትን ወደ ስራ ለማስገባት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም