ለገዢ ትርክት ግንባታ የሚያግዝ ዘመኑን የዋጀ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት አሰራር ያስፈልጋል

ወልቂጤ፤ መጋቢት 17/2017 (ኢዜአ):- ለገዢ ትርክት ግንባታ የሚያግዝ ዘመኑን የዋጀ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት አሰራር መቅረጽ እንደሚያስፈልግ

በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) ገለጹ።

May be an image of 2 people, dais and text

"ውጤታማ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ለገዢ ትርክት" በሚል መሪ ሃሳብ ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሰጠ የሚገኘው ስልጠና እንደቀጠለ ነው።

በዛሬው የሶስተኛ ቀን ውሎው ስልጠናው ''መሰረታዊ የመሪነት ጥበብ እና አገልጋይ መሪ'' በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተሰጠ የሚገኘው።

ስልጠናውን የሚሰጡት በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር ) እንዳሉት ለገዢ ትርክት ትኩረት የሚሰጥ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት አመራርና ባለሙያ ለመገንባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ሚዲያው ለህዝብ ጥቅም የሚሆኑ ገዢ ትርክቶችን እያጎለበተ በሚያስተሳስሩ አጀንዳዎች ላይ ማተኮር እንዳለበት አንስተው ይህም ሀገራዊ የልማትና ሁለንተናዊ ብልጽግና ግቦችን ለማሳካት አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።

ዘርፉ ለተግባቦት ቅድሚያ የሚሰጥ እንዲሁም ለልማት የሚያነሳሳ ሲሆን ለሀገር ልእልና ያለው ፋይዳም ትልቅ ነው ብለዋል።

ለዚህም በተገቢው መምራትና ማብቃት እንዲሁም ዘመኑን የዋጀ ለገዢ ትርክት የሚያግዝ አሰራር መቅረጽ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

መረጃን በወቅቱና በኃላፊነት ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ትልቅ ተልዕኮ አንግቦ የሚሰራ ሊሆን ይገባል ያሉት ኃላፊው የጋራ አጀንዳና መልዕክት ቀርጾ ለሀገረ መንግሥትና ተቋም ግንባታ የበኩሉን ማበርከት ይኖርበታል ሲሉም ተናግረዋል።

በክልሉ ዘርፉን ለማሳደግና ተቋማዊ ግንባታን ለማጎልበት በልዩ ሁኔታ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት የጽህፈት ቤት ኃላፊው የዘርፉ አመራርና ባለሙያ ይህን ታሳቢ አድርጎ ራሱን በክህሎት ማብቃት እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል።

በስልጠናው መድረክ የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘሪሁን እሸቱ እና የክልሉ አመራር አካዳሚ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ብላቱን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን እንዲሁም የማህበረሰብ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን አመራር አባላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም