የከተሞቹን መልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የከተሞቹን መልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እየተሰጠ ነው

አዳማ፤ መጋቢት 17/2017 (ኢዜአ፦ በድሬዳዋና አዳማ ከተሞች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የከተሞቹ የስራ ሀላፊዎች ገለጹ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን፤ የከተማው ነዋሪ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ በቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ከድሬዳዋ አስተዳድር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመሆን አገልግሎቱን ወደ ዲጂታል የመቀየርና ተገልጋዩ ካለበት ሆኖ የተሻለና ፈጣን አገልግሎት ማግኘት እንዲችል እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይም ከመሬት አስተዳደር፣ ከገቢዎች፣ ከከተማ ፀጥታና ደህንነት ጋር በተያየዘ እንዲሁም የዕለት ተዕለት የህዝብ አገልግሎት የሚበዛባቸው የአስተዳደሩ ሴክተር ተቋማት አገልግሎቶችን የማዘመን ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በእነዚሁ ተቋማት በአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ጠቅሰው፤ ይህም ሌብነትና ብልሹ አሰራርንም ለመከላከል እያገዘ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ነዋሪዎች ካሉበት ሆነው የንግድ ፍቃድ እንዲያድሱና የግንባታ ፍቃድ እንዲያገኙ በማድረግ አገልግሎቱን ማሳለጥ መቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህም የከተማውን የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ ማድረግ አስችሏል ብለዋል።
በተመሳሳይ የአዳማ ከተማ የስራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ፉፋ ገርማማ በበኩላቸው በከተማዋ አገልግሎቶችን በማዘመንና ዲጂታል በማድረግ ተገልጋይ ሳይቸገር የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉን ተናግረዋል።
በከተማዋ ተገልጋዮች ካሉበት ሆነው ሳይንገላቱ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰው፤ በተለይም 'ጋዲሳ ኦዳ' በሚል የአንድ ማዕከል አገልግሎት መሰጠቱ የተሻለ ውጤት እይስገኘ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም አብዛኛው ተቋማት አንድ ቦታ ሆነው የተቀናጀና የተናበበ አገልግሎት በመስጠት የህዝብ ቅሬታን ደረጃ በደረጃ መፍታት ማስቻሉን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት የስራ አጥ ወጣቶች ምዝገባ ዲጂታል ከማድረግ ባለፈ በስማርት ሴኩሪቲ የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ ሁኔታዎችን የመከታተል፣ የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶችንም ከወረቀት ንኪኪ ነፃ የማድረግ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ዲጂታል አገልግሎቱ ተገልጋዩ የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር፣ የትራንስፖርት ስምሪትና የትራፍክ ቅጣት ክፍያ አሽከርካሪዎች ካሉበት ሆነው በተንቀሳቀሽ ስልክ እንዲከፍሉ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።