የጂኦሳይንስ ላቦራቶሪ ማዕከል ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በአዲስ መልክ ሊደራጅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጂኦሳይንስ ላቦራቶሪ ማዕከል ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በአዲስ መልክ ሊደራጅ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት እና ከኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ለጂኦሳይንስ ላቦራቶሪ ማዕከል መልሶ ለማደራጀት ስራ የትብብር ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
የመልሶ ማደራጀት ስራው ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግበት የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢጃራ ተስፋዬ እና የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሽመልስ እሸቱ ተፈራርመዋል።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የማዕድን ሚኒስትር ሃብታሙ ተገኘ( ኢ/ር) እና ሚኒስትር ዴኤታዎች ተገኝተዋል።
የጂኦሳይንስ ላቦራቶሪ ማዕከል የጂኦሳይንስ መረጃን በማመንጨትና ማዕድናትን በመመርመር ለረጅም ጊዜ እያገለገለ ይገኛል።
ስምምነቱ የጂኦ ሳይንስ መረጃን ለማመንጨት እና የማዕድናት ናሙና መመርመሪያ በመሆን የሚያገለግለውን የጂኦሳይንስ ላቦራቶሪ ማዕከልን መልሶ ማደራጀት የሚያስችል መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በስምምነቱ መሰረት ግንባታውን ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱም ተጠቁሟል።