ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ስዊድን የልማት ትብብራቸውን በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር አደረጉ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 17/2017 (ኢዜአ)፦የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በስዊድን የዓለም አቀፍ ልማት ትብብር እና የውጪ ንግድ ሚኒስቴር ዋና ተጠሪ ዲያና ጃንስ ጋር ዛሬ ውይይት ተወያይተዋል።

ውይይቱ የሁለቱ ሀገራት የልማት ትብብር እና የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።

በዓለም ደረጃ ያለው የፋይናንስ አቅርቦት ውስንነት እና የጂኦ ፖለቲካ ለውጦች ታሳቢ ያደረጉ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ የልማት ስራዎችን ውጤታማነት የማሳደግ ጉዳይም በውይይቱ ላይ አጽንኦት የተሰጠው ነው።

ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ የሀብት መሰብሰብ አቅም የሚያሳድግ፣ የኢኮኖሚ እድገት እና የንግድ አጋርነትንን የሚያጠናክር የልማት ፋይናንስ አቅጣጫ መከተል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ስዊድን በዘላቂ ልማት እና በእሴት ሰንሰለት ልማት ያላትን ሙያዊ ልምድ መጠቀም የሚቻልባቸውን እድሎችም ተመልክተዋል።

ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ስዊድን የኢኮኖሚ ትስስራቸውን ለማጠናከር ፣ የግሉ ዘርፍ ትብብራቸውን ለማሳደግ እና ለዘላቂ እድገት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የሀገራቱ የሁለትዮሽ ትብብር ለዜጎቻቸው ዘላቂ ጠቀሜታን የሚያመጡ እንዲሆን በጋራ እንደሚሰሩም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም